Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ጽምጻቸውን የሚያሰሙበት መርሃ-ግብር ነገ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ በያሉበት ሆነው ለአንድ ሰዓት መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት መርሃ-ግብር ነገ ይከናወናል።

መርሃ-ግብሩ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ንቅናቄውን ያዘጋጁት ከማህበረሰብ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ ሲቪክ ማህበራትና ታዋቂ ግለሰቦች የተወጣጡ ናቸው።

የንቅናቄው አስተባባሪ አቶ ዐቢይ ታደለ ነገ ከቀኑ 10 እስከ 11 ሰዓት ድረስ የሚቆይ “ከኢትዮጵያ እጃችሁን አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ዝግጅት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

መርሃ-ግብሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም አጋርነታቸውን ለማሳየት ተዘጋጅተዋል።

በአንድ ሰዓቱ መርሃ-ግብር “ብሔራዊ ክብር በሕብር”፣”እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ”፣”የውጭ ሃገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማክበር አለባቸው”፣”የውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነታቸውን ያቁሙ”፣”የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከማከናወን የሚያግደን ሃይል የለም” እና “ምርጫውን ማካሄድ የውስጥ ጉዳያችን ነው” የሚሉ ሐሳቦችን ያዘሉ መልዕክቶች ይተላለፋሉ ተብሏል።

ዜጎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም እንዲሁም በአደባባይ በመውጣት መልዕክታቸውን ማስተላለፍ እንደሚችሉ ነው አቶ ዐቢይ የገለጹት።

በተያያዘም ንቅናቄውን በማስመልከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የዲጂታል ፊርማ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ዛሬ ይጀመራል።

በየፊርማ ማሰባሰቡ “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄድ መሆኑን አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ነገ ማለዳ ከታዋቂ ግለሰቦችና አርቲስቶች የተውጣጡ ግለሰቦች በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤምባሲዎች በመሄድ የተዘጋጁ ደብዳቤዎችን እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።

ደብዳቤው የውጭ ሃገራት በኢትዮጵያ የሚያከናውኗቸው መልካም ተግባራት ቢኖሩም በአሁኑ ሰዓት በውስጥ ጉዳይ እያሳዩ ያሉት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የሌለውና እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ የሚል ይዘት ያለው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ የዚሁ ንቅናቄ አካል የሆነ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት ይካሄዳል ያሉት አቶ ዐቢይ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ንቅናቄው የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.