Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚተገበሩ የጥራት ማሻሻያ ስራዎች አስደሳች ናቸው – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል እየተተገበሩ ያሉ የግንባታ ማስፋፊያዎች የጥራት ማሻሻያ ሪፎርም ስራዎች አስደሳች ናቸው ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
ሚኒስትሯ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማና አካባቢው የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።
የእናቶችና ህጻናት፣ ስነተዋልዶና የሰርቶ ማሳያ አገልግሎቶችን፣ ሞዴል ቤተሰቦችን በመጎብኘት በጤና ኬላው የሚሰጡ ትምህርቶች አበረታች አተገባበርን መመልከታቸውንም ጠቅሰዋል።
የአሶሳ ከተማ ጤና ጣቢያ የሚሰጠውን የእናቶች እና የህፃናት ጤና፣ በተለይም ለእናቶች ጤና ቁልፍ በመሆኑ የተጀመረውን የቀዶ ህክምና፣ የድንገተኛ ህክምና፣ እንደ ቅድመ ማህጸን ካንሰር ምርመራና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራና ክትትል እንዲሁም ሌሎች የጤና አገልግሎቶች መልካም መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተግዳሮቶቹን በመቅረፍ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል እየሰራ ለሚገኘው የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የአሶሳ ዞንና ወረዳ፣ የአጉሻ ጤና ኬላ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የአሶሳ ከተማ ጤና ጣቢያ አመራሮች ባለሙያዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ለህብረተሰቡም ምስጋና አቅርበዋል።
በጉብኝታቸው የአሶሳ ደም ባንክ እና የክልሉ መድሃኒት ኤጀንሲ የደም አቅርቦትን ጨምሮ ከክልሉ አልፈው አጎራባች ኦሮሚያ ክልል  መድሃኒት በማቅረብ ለህብረተሰቡ ጤና መጠበቅ ያሳዩት ቅንጅታዊ አሰራር ተስፋ ሰጭ ናቸው ማለታቸውን ከማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.