Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከል እና መቆጣጠር የሚያስችል የ2 ወራት ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከል እና መቆጣጠር የሚያስችል የሁለት ወራት ንቅናቄ መጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮወ ሃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ ከፋና ዜና መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ንቅናቄው ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎችን በጥብቅ ዲስፒሊን ማስፈጸም እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ይህም አሁን ላይ የስርጭቱን ሁኔታ በተለመደው የአደጋ ምላሽ አካሄድ መፍታት ባለመቻሉ እና የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብሱ ሁነቶች በመኖራቸው የተወሰነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በንቅናቄው መሰረትም የሁሉም ሴክተር ሃላፊዎች የወጣውን መመሪያ 30 በትክክል የማስተገበር ሃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ዶክተር ዮሃንስ፤ ሃላፊነታቸውን የማይወጡ አካላትም ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡

በተለይም  ቫይረሱ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይ በቅንጅት እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ በመዲናዋ አካላዊ ርቀትን የመጠበቁ ምጣኔ 28 ነጥብ 9 በመቶ ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ሃላፊው በቀጣይ ምጣኔውን ወደ 35 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አሁን  ላይ ያለውን የመመርመር አቅም ማሳደግ እና ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ላይ  በቅንጀት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በቫይረሱ ተይዘው ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል ለሚገቡ ታካሚዎች የመተንፈሻ መሳሪያዎችን አና የኦክስጅን  አቅርቦት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን  ዶክተር ዮሃንስ አብራርተዋል።

በመዲናዋ እስካሁን ለ130 ሺህ ሰዎች የኮሮና ክትባት መስጠት መቻሉን የገለጹት ሃላፊው  በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ለ300 ሺህ ሰዎች ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለሁሉም ጽኑ ታማሚዎች የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ሟሟላት ከባድ መሆኑን የሚናገሩት ሃላፊው፣ ከዚህ ይልቅ መከላከሉ ላይ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡

በተለይም ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱ ትውልድ የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች በትክክል ተግባራዊ በማድረግ እራሱን እንዲጠብቅ ዶክተር ዮሃንስ አሳስበዋል፡፡

ንቅናቄው የታሰበለትን አላማ ይመታ ዘንድም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሽታው የደረሰበትን አስከፊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.