Fana: At a Speed of Life!

እንደአባቶቻችን ከተባበርን ማንም አይደፍረንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “እንደአባቶቻችን ከተባበርን ማንም አይደፍረንም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

በአንድነት ፓርክ እየተካሄደ ባለው የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የአማራ ባህል ማዕከል ግንባታ ማስጀመሪያ ዝግጅት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስደንቁ የማዕድን ክምችቶች ቢኖሩም ከመተያየት ባለፈ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በወንድማማች ፓርክ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ሳምንት የሚያስደንቅ ባህልና ምግብ መቅረቡንም ተናግረው፤ የትብብር፣ የመጎራረስ፣ አብሮ የመቆም፣ የመደጋገፍ ሁኔታ ላይ ካልተሰራ በስተቀር አሁን ባለው ሁኔታ እንዲሁ በመተያየትና በማዘን ከመኖር ያለፈ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል አስገንዝበዋል።

“ይህ እንዳይሆን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭም በብዙ የሚሰሩብን ሃይሎች አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን የሃብታም ልጅ በጀርባዋ በተሸከመች ደሃ እናት መስለዋታል።

“ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንፈልጋለን የሚሉ ብዙዎች እንዲሁ ትልቅ እያልናችሁ ኑሩ እንጂ ትልቅ መሆን እምብዛም አያስፈልጋችሁም ይላሉ” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ “የእነሱን ልጆች አዝለን ማሳደግ ግዴታችን እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጥያቄዋ በህብረት መልማትና መበልጸግ እንደሆነ ገልጸው፤ “የሃብታም ልጆችን እያዘልን ማሳደግ ሳይሆን እርስ በርስ ተጎራርሰን ተደጋግፈን በህብረት ማደግ፣ መለወጥና ሲተርፈን ሳናዝል መደገፍ የምንችልበት ቁመናን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል እምነት ስላለን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ብልጽግና ይገባዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብልጽግና መጓጓት፣ መሻትና መፈለግ በመሆኑ ጉዞው ፈታኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም መተባበር ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

“እንደአባቶቻችን ከተባበርን ማንም አይደፍረንም” ሲሉ ገልጸው፤ “ነጻነታችንና ክብራችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ እንድንወስድ በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመተሳሰብ በመደመር መንፈስ አንድ ሆነን ኢትዮጵያን አበልጽገን ለአፍሪካ ምሳሌ እንሁን” ሲሉ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.