Fana: At a Speed of Life!

ከሚያለያዩን ውስን ጉዳዮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን እልፍ ጉዳዮቻችን ላይ በጋራ እንሠራለን – ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለአማራ ባህል ማዕከል መገንቢያ የሚሆን 42ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አስረክበዋል።

የአማራ ልማት ማህበር በአዲስ አበባ ለሚያስገነባው የአማራ ባህል ማዕከል ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐግብር በአንድነት ፓርክ ተካሂዷል ፡፡

ልማት ድንበር የለውም፣ ልማት የሁላችንም አንድነት እና መደጋገፍ ይጠይቃል  ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ÷ የተለያዩ  የልማት ማህበራት የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ከማሟላት በላይ ለአንድነትና አብሮነት ዋልታ ናቸው ብለዋል፡፡

”ሺህ ሆነን እንደ አንድ፤ አንድ ሆነን እንደ ሺህ” የሚለው የአልማ መልዕክትም ለአብሮነታችን መቆሙን ያመላክታል ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የልማት ተቋማት ተቀራርበው እንዲሠሩ፣ ሕዝቦቻቸውን እንዲያቀራርቡ እና በጋራ የሀገር ግንባታ ሂደት ጉልበት እንዲሆኑ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡

ከሚያለያዩን ውስን ጉዳዮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን እልፍ ጉዳዮቻችን ላይ በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ÷ በዚህም አዲስ አበባንም የኢትዮጵያዊያን የልማት እና የቱሪዝም ማእከል ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አገኘሁ ተሻገር  በበኩላቸው ÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባሕል ማእከሉ እውን እንዲሆን መገንቢያ ቦታ በመስጠቱ በክልሉ ህዝብ ስም አመስግነዋል፡፡

የባሕል ማእከሉ  የአማራ ሕዝቦችን ቱባ ባሕል እና ትውፊት የሚታይበት፣ የማንነታቸው መገለጫ ሆኖ እንዲገነባ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አቶ አገኘሁ መናገራቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሬተሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.