Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች ላይ የተጣለው የቪዛ ክልከላ አግባብነት የሌለው ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች ላይ ያሳለፈው የቪዛ ክልከላ ውሳኔ አግባብነት የሌለው መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች ላይ የቪዛ ክልከላ ውሳኔ ማሳለፉ ታወሳል፡፡

መግለጫው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ማበረታቻ እና የፀጥታ ድጋፍ ለማቋረጥ መወሰኗንም አስታውሷል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ለመፍጠር ያሳለፈው የቪዛ ክልከላ አግባብነት የሌለውና አሳዛኝ መሆኑን ገልጿል፡፡
አሁን የተላለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አወንታዊና ገንቢ በሆነ መልኩ መስራት በጀመረበት ወቅት መሆኑን አንስቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሃገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ትሩፋቶችን ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሃገራዊ ምርጫ ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት የተወሰነ የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
6ኛው ሃገራዊ ምርጫ አካታች ለሆነ ፖለቲካዊ ውይይት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ያለው መግለጫው፥ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እንጅ አላስፈላጊ የሆነና በምርጫው ላይ ጥላ የሚያጠላ ውሳኔን አይጠብቅምም ነው ያለው፡፡
ኢትዮጵያ በፈተና ጊዜ አጋሯ ከሆነችውና ከወዳጅ ሃገር አሜሪካ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያነሳው ሚኒስቴሩ፥ የቪዛ ክልከላውን ጨምሮ መሰል እርምጃዎች የሃገራቱን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ሊጎዳው እንደሚችልም ነው የገለጸው፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን የኢትዮጵያን መንግስት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር በእኩል አይን ለማየት የተሞከረበት መንገድ እጅግ እንዳሳዘነውም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
መንግስት አሃራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከህዝብ ጋር ሲሰራ መቆየቱን በማውሳትም፥ ይህም ከውጭ ስለተገፋ ሳይሆን አካሄዱ በሃገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ትክክለኛ መንገድ ሆነ ስላገኘው እንደሆነም ነው ያነሳው፡፡
መንግስት ከዚህ ቀደም እንደገለጸው ሁሉ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገው ሙከራ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያም የውስጥ ጉዳይዋን የምታስተዳድርበት መንገድ ሊነገራት አይገባምም ነው ያለው፡፡
በትግራይ ክልል ተፈጽሟል ከተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ መንግስት በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ አካላትን ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.