Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ ከእንግሊዝ የድርቅ መከላከል እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዝ የድርቅ መከላከልና የሰብዓዊ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ኒክ ዳየር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ትግራይ ክልልን የተመለከቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፎች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየተደረገ ስለሚገኘው ድጋፍን ጨምሮ በክልሉ ስላለው ሰፊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎች ለልዩ መልዕክተኛው ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ዙር 4ነጥብ5ሚሊየን እና በሁለተኛ ዙር ደግሞ 2ነጥብ9 ሚሊየን ሰዎችን ፍላጎት ያገናዘበ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦቶች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልፀው፤ ሶስተኛው ዙርም በቅርቡ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት የተፈናቃይ ወገኖችን ችግሮች ለመቅረፍ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተደራሽነትን ለማስፋት እየተደረገ ስላለው ጥረትም ገለጻ አድርገዋል፡፡

በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ አካላትየጋራ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል አበረታች እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም መሰል ምርመራ በማካሄድ ተሳታፊ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ማንሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ ክልሉን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በውይይታቸው ማጠቃለያ በሁለቱ አገራት መካከል የቆየውን ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በማውሳት፣ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽዕኖት ሰጥተው አንስተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.