Fana: At a Speed of Life!

በአውስትራሊያ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ  ውይይት አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውስትራሊያ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያና በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሄደዋል።
በውይይቱ መግቢያ ላይ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሙክታር ከድር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደሩ በተለይም ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ጥፋት ተከትሎ የተወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃና ሂደቱ ያለበትን ደረጃ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅና ከሱዳን መንግሥታት ጋር እየተካሄደ ያለውን ድርድርና የግድቡ ግንባታ አሁን የደረሰበትን ደረጃ፣ እንዲሁም 6ኛው ብሔራዊ ምርጫን ለማከናወን እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በሚመለከት መረጃ በመስጠት የመንግስትን አቋም ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት የህወሓት ቡድን በሃገሪቱ ላይ የፈጸመው ጥፋት በፍጹም ይቅር የማይባል ወንጀል መሆኑንና መንግስት የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በቡድኑ ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው አካላት በሃገሪቱ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ መከላከል ይገባል ብለዋል።
በህወሓት ደጋፊዎች አማካኝነት እየተሰራጩ ያሉ የሃሰት መረጃዎችን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ይህንንም ለማክሸፍ በዳያስፖራ አባላት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ፣ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ አንዳንድ ምዕራባውያን ሃገራት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት አዛዥ ናዛዥ ለመሆን እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ከዚህ በፊት የጀመሯቸውን የድጋፍ ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የህወሓት ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ዙሪያ እያሰራጩ ያሉትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመከላከልና በብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ የሚሰሩ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሰነዘሩ ሲሆን ÷ራሳቸውንም የመፍትሄው አካል በማድረግ በዳያስፖራ ተሳትፎ የሚሰሩ ተግባራትን ለይተው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገቡ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.