Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የጣለችው የቪዛ ክልከላ በግዳጅ ፖሊሲ ለማስቀየር የተወሰደ እርምጃ ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች ላይ የጣለችው የቪዛ ክልከላ ሀገሪቱን በግዳጅ ፖሊሲዋን ለማስቀየር የተወሰደ እርምጃ ነው ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የሰላምና ደህንነትና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንዳሉት፥ በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥረት እያደረገ ያለውን መንግስት ከመደገፍ ይልቅ እቀባ መጣሏ የራሷን ጉዳይ ለማስፈጸም የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ነው ብለዋል ።
የጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪና ተመራማሪው ዶክተር መሳይ ሀጎስ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ምልክት አድርጎ እራሱን የሚወስደው የአሜሪካ መንግስት፥ ሲታይ ለሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ በተግባር ግን በጣልቃ ገብነት ከኢራቅ እስከ ሊቢያ እንዲሁም አፍጋኒስታን ሀገረ መንግስት አፍርሶ ቆሞ አልቃሽ የሆነ ከራሱ ጥቅም አንጻር ብቻ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚታትር ብለውታል፡፡
ለዚህም መንግስት በህግ ማስከበር ዘመቻው እንዴትና ለምን ተገዶ እንደገባ አሁንም የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በዝርዝር ዋሽንግተን ላይ ተጽእኖ በሚያሳድሩ ተዋናዮች በኩል የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይኖርበታል ነው ያሉት ።
የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና አማካሪው ዶክተር ሞገስ ግርማ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ መብቶች መከበር ቁርጠኛ ሆኖ አቋሙን እያሳየ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የቪዛ ክልከላው አሜሪካ በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ጫና ምክንያት የወሰደችው እርምጃ ሊሆን ይችላል ብለዋል ።
ለሰብአዊ መብቶች ከንግግር በዘለለ ተግባሩን የማታውቀው ዋሽንግተን በመሰል ህግና ስርአት አስከብሩ ሰበብ ድንበራቸውን የጣሰችባቸው እና ሉዓላዊነታቸውን የደፈረችባቸው ሀገራት ዛሬ ላይ ከሰብአዊነት ይልቅ ኢ ፍትሃዊነት የነገሰባቸው መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ከአሜሪካ መንግስት በኩል የተላለፈው የቪዛ ክልከላ ዝርዝር ሌሎች ሀገራት ውስጥም ተመሳሳዩን እርምጃ እንዲደግሙት የሚወተውት እንደመሆኑ መንግስት የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ለአሜሪካ ጥቅም ሳይሆን ለዜጎቹ ደህንነት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል ።
በአጠቃላይም ምሁራኑ ከምጣኔ ሀብትና ደህንነት ድጋፍ መቋረጥ ተጽእኖ አንጻርም የባለ ድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር በቅንጅት በመስራት ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በሀይለየሱስ መኮንን
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.