Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያዊያን ለመላው አፍሪካ የነፃነት ቀንዲል ሆናን እንድትዘልቅ በጋራ እንረባረብ – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

 

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን 58ተኛ ዓመት የአፍሪካ ህብረት የምስረታ መታሰቢያ በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የመላው አፍሪካውያን የአንድነት ጥላ ምልክት ለሆነው የአፍሪካ ህብረት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ያሉት አቶ ደመቀ የአፍሪካ ቀን በየአመቱ ሲዘከር ሃገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን እና ክብሯን በቀዳሚነት አስጠብቃ መዝለቋ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ደማቅ ታሪካዊ ትርጉም ይቸራልዋል ነው ያሉት።

ከ125 ዓመታት በፊት በወራሪ ሃይል ሃገራችንን በቅኝ የማሳደር ቀቢፀ ተስፋን ተከትሎ፤ የቁርጥ ቀን ጀግኖቻችን ባደረጉት አኩሪ ተጋድሎ የአድዋ ድል ባለቤት የመሆን ዘለዓለማዊ ዕድል ተጎናፅፈናል ሲሉ ነው የገለጹት።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ቀንን የምናከብርበት ታሪካዊ ምክንያት እንደ አህጉር በፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሎ የተመዘገበ አኩሪ ድል ለመዘከር ሲሆን፤ መቼም ቢሆን በውጭ ኃይሎች ጫና የማንበርከክ ስለመሆናችን ህያው ማረጋገጫ ነው።

በዚህ ወቅት በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ እያማተሩ በሉዓላዊነታችን ላይ ለሚሰነዘሩብን ድፍረት አዘል ጫናዎች እንደማንንበረከክ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል ያሉት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያውያን በአንድነት፥ በመከባበር እና በአሸናፊነት መርሆዎች በዓለም አቀፍ አውድ በነፃነት እና በተወዳዳሪነት ፀንተን እንቀጥላለን ብለዋል።

የድል አድራጊነት ወኔያችንን በማጥበቅ ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜያት ለመላው አፍሪካ የነፃነት እና የኩራት ቀንዲል ሆና እንድትዘልቅ በጋራ እንረባረብ በማለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.