Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድር ትደግፋለች – አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት የሚካሄደውን የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሦስትዮሽ ድርድር እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን ገለጹ።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ካላት ትልቅ ሚና አኳያ የውስጧን ሰላም በማስጠበቅ የቀጠናውን ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ልትመራ እንደሚገባትም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

አምባሳደር ጀምስ ፒቲያ ሞርጋን እንደገለጹት የናይል ውኃ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብት በመሆኑ ሁሉም ያለምንም ችግር ሊጠቀምበት ይገባል።

በውኃው ላይ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ልማታዊ ጎናቸው መታየት አለበት ያሉ ሲሆን፥ ችግሮች ካሉም ሀገራቱ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚነሱ ውዝግቦችም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሦስቱ አገራት ወደ ዘላቂ መፍትሄ መምጣት እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።

የአፍሪካ ኅብረት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ቁመና እያለው ለመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ ለሌላ አካል ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ አያስፈልግም ብለዋል።

አፍሪካ ኅብረትም የታዛቢነት ሚና ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሥልጣን እንዳለው በመረዳት ሁነኛ መፍትሄ ለመሥጠት መሥራት እንደሚገባውም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኅብረቱ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህም እውን ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል “ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሠላም አዋላጅ ነች” ያሉት አምባሳደሩ፥ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሠላም ግንባታ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰላፊ ሀገር ናት ብለዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ተስፋ ሳትቆርጥ ሀገራቸው አሁን ላለችበት ሰላምና መረጋጋት እንድትደርስ አበርክቶዋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ የአየር፣ የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን የመክፈትና የማጠናከር ሥራ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ይህንንም በተመለከተ ከሚመለከተው የኢትዮጵያ ተቋምና ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎ የመግባቢያ ሥምምነት ሠነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ኢትዮጵያ በአካባቢው ካላት ሚና አኳያ ውስጣዊ ሰላሟን በማስጠበቅ የቀጠናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በቀዳሚነት ልትመራ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ቀጣናው የሚከተለው ነጻ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣናውን በምጣኔ ሃብት ማስተሳሰር ከቻለች የቀጠናው አገራት ወደ ልማትና እድገት የመምራት እድሏ ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት አገግማ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች እንደምትገኝ የዘገበው ኢዜአ ነው።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.