Fana: At a Speed of Life!

የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በመዘግየቱና አስፈላጊው ዝግጅት ከተጠናቀቀ ቀኋላ ቅያሬ ቦታ ይዘጋጅ መባሉ ቅሬታ ፈጥሮብናል – ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በመዘግየቱና አስፈላጊው ዝግጅት ከተጠናቀቀ ቀኋላ ቅያሬ ቦታ ይዘጋጅ መባሉ ቅራኔ አሳድሮብናል ሲሉ የሚዛን አማን ነዋሪዎችና የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ገለጹ ።

በሃገሪቱ እንዲገነቡ ባለፈው ዓመት በዕቅድ ከተያዙት 5 የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ በመንግስት ዕቅድ ከመያዙ በፊት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የግንባታ እንቅስቃሴው ከተጀመረ አምስት ዓመት ቢያስቆጥርም ስራው እስካሁን ባለመጀመሩ ማዘናቸውን የሚዛን አማን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ለግንባታው ስንል ይዞታችንን ለቀናል የገንዘብ ድጋፍም አድርገናል የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፥ በጉጉት የጠበቁት ፕሮጀክት ባለመጀመሩ ቅሬታ አሳድሮብናል ሲሉ ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር በበኩሉ፥ የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው መዘግየቱ ሳያንስ አስቀድመን አስፈላጊውን የቦታ ዝግጅት ካደረግን በኋላ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የቦታ ለውጥ ይደረግልኝ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ አሳዛኝ ነው ሲል ገልጿል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ የሚሆን 4ኪሎ ሜትር ቦታ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ሆኖም ከ1ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ከተነሱ በኋላ ለተነሽዎችም ከህብረተሰቡ ገንዘብ በመሰብሰብ 30 ሚሊየን የሚጠጋ የካሳ ገንዘብ ከተከፈለ እና ቦታውም በባለሙያዎች ተጠንቶ ጨረታው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ድርጅቱ ሌላ ተቀያሪ ቦታ ይዘጋጅ የሚል ጥያቄ ለክልሉ ማቅረቡ ተቀባይነት የሌለውና ህብረተሰቡን ያስቆጣ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ግንባታው የዘገየው በጨረታ ምክያት መሆኑን ገልጿል።

ጨረታው ተቀባይነት ካገኘና ቦታው ጥናት ተደርጎበት ዝግጁ ከሆነ በኋላ የቦታ ቅያሬ መጠየቅ ለምን አስፈለገ ስንል የጠየቅናቸው የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ አቶ እስክንድር፥ የፕሮጀክቱ ዋጋ ውድ በመሆኑ ዋጋውን ለመቀነስ የሚያስችል አማራጮች ካሉ ለማየት ምክረ ሀሳብ አቀረብን እንጂ የግድ የቦታ ለውጥ ይደረግ አላልንም ሲሉ ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት የድርጅቱን ጥያቄ ውድቅ በማድረጉም ያለው አማራጭ በተያዘው ዋጋ ስራውን ማስኬድ እንደሆነ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ገልፀዋል።

በተስፋዬ ምሬሳ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.