Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)”አዲሷን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዳረሻ ኢትዮጵያን እናስስ” በሚል ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና የአሜሪካ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎች በሚመለከታቸው አካላት  ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ መንግስት ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠርና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባትም የንግድ ህግ ማሻሻያ መደረጉንና የኢንቨስትመንት አዋጅ መውጣቱን ተናግረዋል ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር  አህመዲን መሐመድ ÷ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን የዘርፉን ማሻሻያዎች በማድረግ የዲጂታል መሰረት እየጣለች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” የማድረግ እቅድ ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካሪ ሜሪያም ሰይድ ኢትዮጵያ ከመንግስት መር ኢኮኖሚ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ ኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተዋናይ እንዲሆን ለማድረግም የንግድ ስራ ቅልጥፍና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አማካሪዋ የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ስራ፣ የዲጂታል ክህሎት ግንባታ፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ጥበቃ፣ የግለሰብ የመረጃ ጥበቃ አዋጅ ለዘርፉ መደላልድል ለመፍጠር እየተሰራባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ማሻሻያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ መቅረቡን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.