Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በመኸር ወቅት የክልሉን አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ልማት ስራ እንዲገቡ ለማስቻል መንግስት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን የተቀናጀ የማቋቋምና ወደ እርሻ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ግብርና ሚኒስቴር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅንጅት ባደረገው እንቅስቃሴ በክልሉ ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ እንዲሸፈን በማድረግ የክልሉ ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ርብርብ በመደገፍ ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ገልፀዋል፡፡
እስካሁን በተደረገው ድጋፍና ርብርብ የዕቅዱ 70 በመቶ የሚሆን መሬት በመኸር እርሻ መሸፈን የሚያስችል እንቅስቃሴ የተደረገ መሆኑን ገልጸው ለዚህ የሚያስፈልግ ግብዓት መቐለ ማዕከላዊ መጋዘን እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም በክልሉ በተደራጁ የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነትም ወደ ወረዳዎች በማጓጓዝ ለያንዳንዱ አርሶ አደር የማድረስ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የክልሉን የመፈጸም አቅም ከፍ በማድረግ ለአርሶ አደሮች የቴክኒካል ድጋፍ በመስጠት ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንዲችሉ ለማብቃት የመስክ ስራ ተሽከርካሪ፣ የቢሮ ቁሳቁሶች፣ ኮምፕዩተሮችና ሌሎች ቁሳቁሳቁሶችና ፋጻሚ ባለሙያዎች በማሰባሰብ ስልጠና መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
የማዳበሪያና የምርጥ ዘር መግዣ እጥረት ችግሩ ለመፍታትም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በማስተባበር ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልገው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ፍላጎት በማሟላት ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የድጋፍ በጀት እየተሰበሰበ ዕቅዱ ማሳካት የሚያስችል ግብዓት ገዝቶ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.