Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ ሊሻሻል ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ ሊሻሻል መሆኑ ተገለጸ።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ክፍያ ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ የዳኝነት የክፍያ ማሻሻያ ደንብ ከ68 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው።

ደንቡ ፍርድ ቤቶች ለሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣኝ ገቢ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ክፍያው ወቅቱን ያላገናዘበ በመሆኑ አገልግሎቱን ለማሻሻል፣ መሰረተ ልማቱን ለመገንባትና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነቱ እንዳያድግ አድርጓልም ብለዋል።

በመሆኑም አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ደንብ የህብረተሰቡን የመክፈል አቅምና ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ባገናዘበ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።

የቀደመው የአገልግሎት ክፍያ ደንብ ከፍርድ ቤቶች የመዝገብ ግልባጭ ለመውሰድ ሃምሳ ሳንቲም የሚጠይቅ ሲሆን፥ ይህ ክፍያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የአንድ የወረቀት ሂሳብ እንኳን የማይሸፍን መሆኑን ፕሬዝዳንቷ አስረድተዋል።

በፍርድ ቤቶች እየመጡ ያሉ ጉዳዮች ውስብስብና ሰፊ በመሆናቸው ይህንን መሸፈን የሚያስችል ገቢ ስለሚያስፈልግ የማሻሻያ ረቂቁ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

እንደኢዜአ ዘገባ በየዓመቱ የሚመጡ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ከ7በመቶ በላይ እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ለመጨረሻ ጊዜ ዛሬ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት ግብአት ታክሎበት በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።

የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተቃኘና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በርካታ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፥ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ደንብ የዚህ አንዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲሱ ረቂቅ ደንብ በአገልግሎቶች ተመጣጣኝ የዳኝነት ክፍያን እንዲኖር፣የዳኝነት ክፍያን ፍርድ ቤቶች እንዲያስተዳድሩት፣ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.