Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመመከት እንደሚሰሩ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመመከት እንደሚሰሩ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ 500 ያክል ተሳታፊዎች በተገኙበት “ኢትዮጵያ በአዲስ መንገድ ላይ” በሚል መሪ ቃል ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ መክፈቻ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አገራችን አሁን የገጠሟትን ፈተናዎች ለማክሸፍ በአገርው ውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ በተቀናጀ መልኩ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በበኩላቸው፥ አሁን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱብን ዘመቻዎች በራሳችን አቅም ከምንገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ፕሮጀክቱን ተባብሮ ማጠናቀቅ ብዙ ጫናዎች እንደሚቀንሳቸው ተናግረዋል።

የግንባታ ሂደቱ 80 በመቶ ለደረሰው ይህ ታላቅ ግድብ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉም ነው የጠየቁት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሲሊያና ሽመልስ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ባደረጉት ገለጻ፥ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቦርዱ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከአሁን ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በተለየ ቦርዱ ከፍተኛ በጀት ከመንግስትም ከለጋሽ አገራትና ድርጅቶች አግኝቶ ለምርጫው ስኬታማነት እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።
ምርጫው 200 ያክል የግል ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉብት ገልጸው፥ ይህም ካለፉት ምርጫዎች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የማህበራት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎችም ከአገር ውስጥም ከውጭም የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማናጋት እየሰሩ ያሉትንና ያልተገባ ጫና እያደረጉ ያሉትን ኃይሎች ከምንጊዜውም በላይ እንደሚታገሏቸው ቃል ገብተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር እና እየተሰነዘረ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቋቋም በተደራጃ መልኩ መንቀሳቀስ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል።

ውይይቱን ያዘጋጁት አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፓራ ሶሳይቲ፣ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች፣ ኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ማዕከል፣ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሀይል እና ሌሎች ተቋማት ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.