Fana: At a Speed of Life!

በኖርዌይ የሚኖሩ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃገራትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ አካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኖርዌይ ኦስሎና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኤርትራ ኮሚዩኒቲ በጋራ በመሆን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በኦስሎና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኤርትራ ኮሚዩኒቲ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ሰሞኑን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም በኦስሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመገኘትነው የተቃውሞ ሰልፉን ያካሄዱት

በዕለቱ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሲቪል ማህበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ ደስታ ÷ የአሜሪካ ሰኔት (S.Res 97) በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፥ የሀገሪቱ መንግሥት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የስራ ሃላፊዎች ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉንና በሃገሪቱ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባቱ ከሉዓላዊነት ጋር የሚፃረር አደገኛ አካሄድ መሆኑን ሠልፈኞቹ በጽኑና በአንድነት እንደሚያወግዙ ገልፀዋል።
አክለውም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን ሲመጡ “America is back” በማለት ወደ ትክክለኛ የዲፕሎማሲ ጎዳናና ወደ ጥሩ አመራር እንደምትመለስ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የገቡትን ቃል ወደ ጎን በመተው በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ የመግባት ድርጊታቸው መቀጠሉ እጅግ እንዳሳዘናቸውም ነው የገለጹት፡፡
አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን እያራመደች በመሆኑ ይሄንኑ በአፋጣኝ እንድታሻሽል ጠይቀዋል።
ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ላይ በትህነግ በሚነዛው የተሳሳተ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ እንዲነሳ፣ ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከፈረጀቻቸው ድርጅቶች ጋር እንድትደራደር እየቀረበ ያለው ጥሪ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንና በቅድሚያ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪዎች ብላ ከፈረጀቻቸው ድርጅቶች ጋር የምትደራደር ከሆነ ለኢትዮጵያ የቀረበው ከአሸባሪዎች ጋር የመደራደሩ ጉዳይ ከዚያ በኋላ የሚታይ መሆኑንና የአሜሪካ መንግስት የራሱን ፍላጎት የሚያስጠብቁለት መሪዎችን ለኢትዮጵያ ለመምረጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች መሠራታቸው ለዓለም ማህበረሰብ ግልጽ ሆኖ እያለ፣ የአሜሪካ መንግስት ይሄንን ወደ ጎን በመተው በሉዓላዊ ሀገራት ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ የመግባቱ ጉዳይ በቀጠናው ላይ ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮችን የሚያስከትል በመሆኑ ከወዲሁ እጇን ከኢትዮጵያ እንድታነሳ ለአሜሪካ መንግስት የፃፉትን የተቃውሞ ደብዳቤ በእለቱ ኦስሎ በሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ማስረከባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.