Fana: At a Speed of Life!

ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ በ19 የህወሓት አመራርና አባላት ላይ እገዳ ተጣለ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ በ19 የህወሓት አመራርና አባላት በአዲስ አበባ የሚገኙ ቋሚ ንብረቶቻቸው ላይ እገዳ መጣሉን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይል አስታወቀ፡፡

ግብረ ሃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአሸባሪው የሼኔ ቡድን ሲደግፉ የነበሩ 141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናስ ስርአት እንዲቀርጥና ገንዘባቸው እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው፤በአሁኑ ወቅት ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ጋር ተሰልፈው ሀገር ለማተራመስና ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦች፤ ቀደም ሲል ለህዝብና ለሀገር ጥቅም እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ከባድ ሀላፊነት ወደ ጎን በመተው ከፍተኛ ሃብት በመመዝበር በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንብረቶች አፍርተዋል።

በተጨማሪም በፈፀሙት የሀገር ክህደት ወንጀል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እንደነበርም አስታውሷል።

መግለጫው አክሎም፤ እነዚህ ግለሰቦች በአንድ በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶችን በመፈጸም፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሰው የህወሓት የጥፋት ቡድን ጋር በአመራርነትና በአባልነት እየተሳተፉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝብና ከሀገር በመዘበሩት ሃብት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የገነቧቸውን የመኖሪያ ህንፃዎችና ያቋቋሟቸውን የንግድ ድርጅቶች በቤተሶቦቻቸውና በወኪሎቻቻው አማካኝነት በማከራየት በወር እስከ 9ሺህ ዶላር ድረስ ይሰበስቡ ነበር።

ግለሰቦቹ ይህን ከኪራይ የሚገኝ ከፍተኛ ገቢ በህገወጥ መንገድ በመላክ የሽብር ቡድኑን ህልውና ለማስቀጠል ለተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ግዢ እንዲሁም ለሎጀስቲክስ አቅርቦት ከማዋል ባሻገር ንብረቶችን በመሸጥም ጭምር ሃብት የማሸሽ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ እያሉ በተደረገባቸው ጥብቅ የመረጃ ስራና ክትትል ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማቅረብ እግዱ በፍርድ ቤት በኩል እንዲፈጸም መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።

ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱና እንዲታገድ የተደረገባቸው የሸብርተኛው የህወሓት ቡድን አመራርና አባላት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በቅፅል ስሙ ወዲ ወረደ፣ሌተናል ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ በቅፅል ስሙ ፍስሃ ማንጁስ ፣ሜጀር ጀነራል አበበ ተ/ሀይማኖት በቅፅል ስሙ ጆቤ፣ሜጀር ጀነራል ሀልፎም እጅጉ በቅፅል ስሙ ወዲ እጅጉ፣ ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ ግደይ፣ብርጋዴር ጀነራል ሃ/ስላሴ ግርማይ በቅፅል ስሙ ወዲ እንቤተይ፣ብርጋዴር ጀነራል ምግበ ሀይለ፣ ብርጋዴር ጀነራል ተክላይ አሸብር በቅፅል ስሙ ወዲ አሸብር፣ አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ፤አቶ ሀሰን ሽፋ በድምሩ አስራ ዘጠኝ (19) መሆናቸውን የጋራ ግብረኃይሉ ገልጿል።

መግለጫው አክሎም መቀሌ ከተማ ሆነው ለሽብር ቡድኑ መረጃ ሲሰጡ፤ የፋይናንስና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን በድብቅ ሲያቀርቡ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብሶችን በመልበስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ተመሳስለው ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል 14 የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ፤ለሰብአዊ ድጋፍ በመጓጓዝ ላይ የነበሩና እያንዳንዳቸው 20 ሌትር የምግብ ዘይት የያዙ 2200 ጄሪካኖችን የጫነ አንድ ተሽከርካሪ ከእነ ተሳቢው አስገድደው አቅጣጫውን እንዲቀይር በማድረግ፤ በድብቅ ለሽብር ቡድኑ ለመላክ ሲሞክሩ መሆኑን አትቷል።

በተመሳሳይም ሀገር በማፍረስ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ ያለውን የአሸባሪውን የሸኔ ቡድንን እንቅስቃሴ በገንዘብ ሲደግፉ የነበሩ የ141 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የፋይናንስ ስርዓት እንዲቋረጥና በአካውንታቸው ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲታገደ መደረጉንም የጋራ ግብረ ኃይሉ አመልክቷል።

በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞኖች፣ በጅማና በዙሪያው በሚገኙ ወረዳዎች 27 አባላቱም በጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ያመለከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ ለቡድኑ ሊላኩ የነበሩ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶችም በተደረጉ ጥብቅ ክትትሎች በተለያዩ አካባቢዎች መያዛቸውን ገልጿል።

አሸባሪው ሸኔ ባዋቀራቸው ሴሎች ዙሪያ ይደረግ በነበረው ክትትል ለቡድኑ ተገዝተው ሊላኩ የነበሩ 5661(አምስት ሺህ ስድሰት መቶ ስልሳ አንድ) የክላሽንኮቭ ጥይቶች፤ 2000 (ሁለት ሺህ) የብሬን መትረየስ ጥይቶች፤ ሌሎች ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያ የሚውሉ ቁሶችና ሰነዶች እንዲሁም አዘዋዋሪዎቹም ጭምር ቡራዩ፣ ጊንጪና ከአምቦ ወጣ ብላ በምትገኘው ባቢች በተባለች ቦታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለጫ ጠቁሟል።

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ ለሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት የሽብር ተግባር የሚውሉ ህገወጥ ገንዘቦችን ምንጭ በተመለከተ ባደረገው ሚስጥራዊ ክትትል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት እንዲሁም በቶጎውጫሌ እና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር በህገወጥ መንገድ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በቁጥጥር ስር ማዋሉውንም በመግለጫው ጠቁሟል።

በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም አንድ ሚሊየን 267 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፤ ከ900 ሺህ በላይ ዩሮ፤ እንዲሁም 90ሺህ ፓውንድና ከ2 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር ከአስራ ሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር መያዙን አስታውቋል።

በተያያዘ ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተቀሰቀሰውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠርም መነሻውን ጋምቤላ መዳረሻውን አማራ ክልል በማድረግ በኮድ ሶስት የታርጋ ቁጥር አ/አ A25773 አይሱዝ የጭነት መኪና የታሸጉ ውሃዎችንና ሸቀጦችን እንደሽፋን በመጠቀም ሚስጥራዊ ቦታ ሻግ በማዘጋጀት 62 ክላሽንኮቭ ከ36 ካዝናዎች ጋር በድብቅ ለማሳለፍ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ሽብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመፈፀም የሚሞክሯቸው ጥቃቶች እንዲሁም በውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፤ ግጭትና ትርምስ በመፍጠር የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያለሙ መሆናቸውን መላው ህብረተሰብ በመገንዘብ ሴራዎቹን በማክሸፉ ሂደት ከጅምሩ ጥቆማ በመስጠትና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ላበረከተው አስተዋፅኦ የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይሉ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን፤ በቀጣይም የጥፋት ተልዕኮዎቹን ለማክሸፍ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል።

ሽብርተኞችን በገንዘብ የሚደግፍ ማንኛውም አካል ጉዳዩ በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ የጠቆመው የጋራ ግብረ ሃይሉ መግለጫ፤ የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ በሽብርተኞቹ የህዋሓትና የሸኔ ቡድን አባላት የሚቃጣውን ጥቃት እንዲሁም በውጭ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚቀነባበረውን ሴራ ለማክሸፍ በደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል እየተወሰደ ያለውን የተቀናጀና ተከታታይ እርምጃ በመገናኘ ብዙሃን በኩል ለህብረተሰቡ ይፋ የማድረግ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።

ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለጸጥታና ለመረጃ አካላት የተለመደ ጥቆማ መስጠቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.