Fana: At a Speed of Life!

በሃሰት መረጃ ህዝቡን ለማደናገር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ተራ ተግባር ነው – ብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝቡን ለማደናገር የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ተራ ተግባር መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡

ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሾልኮ የወጣ የፓርቲውን ፕሬዚዳንት ንግግር በማስመሰል ተፈብርኮ የተለቀቀውን ድምጽ አስመልክቶ ፓርቲው ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንዳሉት እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሙሉ በሙሉ ሃሰትና የፓርቲው ፕሬዚዳንት በተለያየ መድረክ ላይ ከተናሩት ንግግሮች ተቆራርጦ የተፈበረከ ነው፡፡

አለማውም ህዝቡን ማደናገርና በህዝብና መንግስት መካከል ያለመተማመን እንዲፈጠር ብሎም ውጥረትና ያለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ተግባሩ ተቀባይነት የሌለውና ሃላፊነት በማይሰማቸው አካላት የሚሰራጭ የወረደ ተግባር እንደሆነ መናገራቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህ ተግባርና ከጀርባ ያለው ድብቅ አጀንዳ ላይ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የውስጥ እና የውጭ አካላት እጅ እንደሚኖርም ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

መሰል የሃሰት መረጃዎችን ማሰራጨት ባለፉት ቅርብ አመታት እየተለመደ መጥቷል ያሉት ሃላፊው ህዝቡ መሰረት ከሌላቸውና ምንጫቸው ካልታወቀ መረጃ እንዲጠበቅና መረጃዎችን በጥንቃቄ እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.