Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በሰኔ 14 በተለያዩ ምክንያቶች ድምጽ የማይሰጥባቸውን  አካባቢዎች ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሰኔ 14 በተለያዩ ምክንያቶች የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የማይከናወንባቸውን  የተወሰኑ አካባቢዎች ይፋ አድርጓል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ መስጫ ቀን መሆኑን አሳውቆ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፣ ከዚህም መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የድምጽ አሰጣጡ በእለቱ የማይከናወንባቸው ምርጫ ክልሎች መኖራቸውን እና ምክንያታቸውን በግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል ።

የድምጽ መስጫ ቀን እስኪቃረብም ድረስ እነዚህን ምርጫ ክልሎች ሁኔታ እየገመገመ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ማቅረብ የሚቀጥል ይሆናል።

በዚህም መሰረት

  1. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዚህ በፊት የተጠቀሱት አራቱም (መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሽ እና ዳለቲ) የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ የመስጠት ተግባር አይከናወንባቸውም፣ ቦርዱ ተጨማሪ የአፈጻጸም ሁኔታዎችን ለወደፊት የሚያሳውቅ ይሆናል።
  2. በሶማሌ ክልል 14 ምርጫ ክልሎች ላይ (11ዱ ምርጫ ክልሎች ምርመራ ላይ ያሉ) ሰኔ 14 ቀን 2013 ድምጽ የመስጠት ሂደት ለማካሄድ አስቸጋሪ ይሆናሉ የተባሉ ሲሆን ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ላይ የታየ መጠነ ሰፊ የአሰራር ችግር አለ በሚል የቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ የአጣሪ ቡድን አሰማርቶ የማጣራት ተግባሩን አጠናቋል፣ በዚህም መሰረት የአጣሪ ቡድኑን ግኝት መሰረት አድርጎ ድምጽ መስጠት ሊከናወንባቸው የሚችል ምርጫ ክልሎች ካሉ ለይቶ የሚያሳውቅ ይሆናል።
  3. በኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው ሰባት ምርጫ ክልሎች (ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ) ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ የመስጠት ተግባር አይከናወንባቸውም።
  4. አማራ ክልል ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ስምንት ምርጫ ክልሎች መካከል ድልይብዛ ምርጫ ክልል ላይ ቦርዱ ሰኔ 14 ቀን 2013 ድምጽ መስጠት ሂደት አንዲከናወን ወስኗል። ይህም ከክልሉ መንግስት በተሰጠ ማረጋገጫ መሰረት የመራጮች ምዝገባ በተስተጓጎለባቸው አምስት ምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ያሉ ዜጎች ሌሎች ጣቢያዎች ላይ መመዝገባቸው በመረጋገጡ ነው።

በሌላ በኩል ግን በአማራ ክልል አንኮበር የምርጫ ክልል ድምጽ መስጠት ሰኔ 14 ቀን እንደማይካሄድም ቦርዱ ወስኗል፣ ቦርዱ ይህንን የወሰነው የአርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል ላይ ድምጽ የሚሰጡ ዜጎች ለክልል ምክር ቤት በዚህ ምርጫ ክልል ድምጽ የሚሰጡ በመሆኑ እና በአካባቢው ባለ የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለመመዝገባቸው ነው። በዚህም መሰረት በአማራ ክልል በስምንት ምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን ድምጽ መስጠት ሂደቱ አይከናወንም።

  1. በደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት አራት የምርጫ ክልሎች በተጨማሪ ማጀት መደበኛ የምርጫ ክልል ሰኔ 14 ቀን ድምጽ አይሰጥበትም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በሱርማ፤ በዲዚ፣ በሜኢኔት ልዩ የሚኖሩ ከብሔሩ ውጪ ያሉ ዜጐች ለተወካዮች ም/ቤት በማጀት መደበኛ ላይ ድምፅ ስለሚሰጡ እና የተጠቀሱት ቦታዎች ምዝገባ ስላልተከናወነ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ጉራፈርዳ ላይ ባለው የጸጥታ ችግር የተነሳ የጸጥታ ችግር ሸኮ ልዩ የምርጫ ክልል እና ቴፒ ምርጫ ክልል  ሰኔ 14 ቀን ድምጽ መስጠት አይከናወንም። በዚህም ምክንያት ደ/ብ/ብ/ህ ክልል ሰባት ምርጫ ክልሎች ላይ በእለቱ ድምጽ አይሰጥም።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.