Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ የመልሶ ማገገሚያ እቅድ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ የመልሶ ማገገሚያ እቅድን ይፋ አደረጉ፡፡

እቅዱ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ማህበራዊ አንድነትን፣ መተማመን እና መረጋጋትን መልሶ በመገንባት የነዋሪዎችን ሰላምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሁሉም ደረጃ የሚገኝ የመንግስት አግልግሎትን፣ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ማስገባትም የእቅዱ አንድ አካል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሰብአዊ ድጋፍን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲሁም የግሉን ዘርፍ በተለይም የኢኮኖሚ እና ቢዝነስ እንቅስቃሴውን ዳግም ስራ የማስጀመር አላማ እንዳለውም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዶክተር አብርሃም በላይ፥ በክልሉ ረዘም ላለ ጊዜ በሰብአዊ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ላለመሆን የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያና የተሃድሶ ፕሮግራሙን ማስጀመር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በክልል የሚገኙ መስሪያ ቤቶች ለእቅዱ መተግበርና ወደ ስራ መግባት ሙሉ ሃላፊነቱን እንዲወስዱም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ያስሚን ዎሃብረቢ በበኩላቸው፥ እቅዱ በደረሱ ጉዳቶችና በአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያው ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናት ከተደረገ በኋላ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሂደትም የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ጨምሮ ከፌደራል መንግስት፣ ከተመድ ከተውጣጡ የልማት አጋር አካላት፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከአፍሪካ ልማት ባንክት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት መሳተፈቻውን አንስተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.