Fana: At a Speed of Life!

የሀረር እና የአርታ ከተሞች የእህትማማች ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረር እና የጂቡቲዋ አርታ ከተሞች የእህትማማች ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲ በድሪ የተመራ የልዑክ ቡድን በጂቡቲዋ አርቲ ከተማ በመገኘት በሁለቱ ከተሞች መካከል የእህትማማች ግንኙነታቸውን ማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ሃገራት የሚታየው ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሃገራቱ ጠንካራና ተምሳሌታዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ግንኙነቱን በማጎልበት የጋራ ባህልን ለማሳደግ ከዚህ በበለጠ በትብብር መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የአርታ ከተማ ልዑካን ቡድን በታሪካዊቷ የሃረር ከተማ ጉብኝት እንዲያደርግ ግብዣ አቅርበዋል።

የአርታ ክልል ገዥ መሀመድ ሸሆ በበኩላቸው የዘይላ ሀረር ታሪካዊ የንግድ ትስስር፥ ሀረር እና አርታ የሰላም ከተሞች ምሳሌ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ሁለቱ ከተሞች ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ለትውልድ በማስተማር ይበልጥ በኢኮኖሚ ለመተሳሳር መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

አያይዘውም በግብርና እና በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመለዋወጥ መስራት ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጉብኝቱ ወቅት የሁለቱን ከተሞች ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል በአርታ ከተማ አስተዳደር ለሀረር ባህላዊ ማዕከል ግንባታ የሚያገለግል ቦታ ተበርክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.