Fana: At a Speed of Life!

ማህበሩ በመዲናዋ ያሰባሰበውን ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ከተማዋን ሊያለማበት ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ልማት ማህበር በአዲስ አበባ ያሰባሰበውን ከ300 ሚሊየን ብር በላይ ከተማዋን ለማልማት መወሰኑን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) የ2013 ዓ.ም ማጠቃለያ ኮንፍረንሱን ያካሄደ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ክፍለ ከተሞች 55 ሺህ የማህበሩ አባላት የተሰበሰበውን ገንዘብ ነው ለከተማው ልማት እንዲሆን መወሰኑ የተነገረው፡፡

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩ አዲስ አበባን ሊያለማበት ወስኖ የልማት ግብዓት እንዲሆነው የጠየቀውን መሬት ማስረከቡን አስታውቋል፡፡

‘‘የልማት ቦታ ስንሰጥ በተባለው ልክ እና በተባለው ጥራት እንደሚሰራ እምነቱ አለንና ፣ ሁላችንም ይህንን ትልቅ አላማ ያለው እና ለከተማችን እድገት እና ውበት ለመስራት ከቆረጠው ኦ.ል.ማ ጎን በመቆም በአንድነት ልማታችንን እና ብልጽግናችንን እናረጋግጥ ለማለት እወዳለሁ’’ ሲሉ ወይዘሮ አዳነች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ከንቲባዋ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም፥ ሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች በሚኖሩባት የኦሮሚያ ክልል ኦልማ የቋንቋና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ሳይገድበው ከሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች አባል አፍርቶ፣ አንድነቱንም አጠናክሮ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚነት ሰርቷል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባም በትምህርት እና በሰው ኃይል ልማት ላይ ከሰራው ልምድ እና ግብዓት በማካፈል የእቴጌ መነን አዳሪ ትምህርት ቤት እና የገላን ትምህርት ቤት ሲቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ነው ምክትል ከንቲባዋ የገለጹት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.