Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ለዜጎች አማራጭ ሀሳብን በማቅረብ ላይ በማተኮር መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ለዜጎች አማራጭ ሀሳብን በማቅብ ላይ በማተኮር መንቀሳቀስ እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ፥ በማህበረሰብ ውስጥ የመገለል እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ክፍተቶች መኖር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰናክል መሆናቸውን ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈም እነዚህ ችግሮች ለሃይል ትግል አማራጭ የሚያነሳሱ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፥ የውይይት እና የድርድር መንገድ ያልዳበረበት ስርዓት ለትጥቅ ትግል ቢጋብዝም ወቅቱ ግን ሃሳብን ለህዝብ ሽጦ በሃሳብ የበላይነት መንገስን የሚጠይቅ መሆኑን አውስተዋል።

ለዚህም አበረታች ጅምር ስራዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ የሺዋስ፥ ይህ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ከሀሳብ ተሻግሮ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሊደገፍ እንደሚገባም ያነሳሉ።

ዴሞክራሲ ሂደት ነው የሚሉት አቶ ቀጀላ ደግሞ ወደ ፊት ማየት ለምንፈልገው የተሳካ ሂደት ዛሬ እርሾውን ማዘጋጀት መጀመር አለብን ብለዋል።

አቶ የሺዋስ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ በርካታ የተሻሻሉ ነገሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ይሁን እንጅ ሀሳብን በመሸጥ ውጤታማ አልሆንም የሚሉ የግጭት እና የብጥብጥ አማራጮችን የያዙ ቡድኖች ጭራሽ ጠፍተዋል ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በመወዳደሪያ መድረኩ የሚወጡ ሰዎች የህዝብን ዳኝነት ለመቀበል እራሳቸውን ያዘጋጁ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በምርጫ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ ከመፎካከር ባሻገር በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚነዙ ግጭት ቀስቃሽ እና ጠብ አጫሪ ድርጊቶች የከፋ አደጋ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ከግጭት እና ብጥብጥ ርቆ እኩል የፉክክር ሜዳን ያመቻቸ እንዲሆን ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ፕሮግራሞቻቸውን ለማስተዋወቅ እክል የሚሆኑ መሰናክሎችን ማጥራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡

በዚህ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባልም ነው የተባለው።

በዳዊት በሪሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.