Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሪሼል ኦማሞ ጋር በሁለትዮሽ እና በወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሁም የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቀጣዩ 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

በምርጫው 50 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ መሆኑን፣ ከሃገሪቱ ለመምረጥ የሚችሉ ዜጎች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የምርጫ ካርድ ማውጣቸውን እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመታዘብ መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተም ሱዳን ወደ ኢትየጵያ ሉዓላዊ ግዛት መግባቷን ገልጸው፥ በኢትየጵያ በኩል በሃገራቱ መካከል ቀደም ሲል በተቋቋሙ የጋራ ድንበር ኮሚቴዎች አማካይነት በሰላማዊ መንገድ እልባት ሊያገኝ የሚችል መሆኑን ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተም በኢትዮጵያ በኩል መጀመሪያ የግድቡ የውሃ አሞላልን በተመለከተ ስምምነት ላይ በመድረስ በሌሎች የውሃ ስምምነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ ግን ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱና የሌሎችንም የተፋሰሱ ሃገራት ተሳትፎ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር ቀጥሎ መታየት እንደሚገባው በኢትዮጵያ በኩል የተያዘ አቋም መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

አሁን በአፍሪካ ህብረት በኩል ድርድሩን በየደረጃው በመክፈል ለማካሄድ የቀረበው ሀሳብ ከኢትዮጵያ አቋም ጋር የሚስማማ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ምንም አንኳ ኢትዮጵያ የውሃ አሞላሉን በተመለከተ ከግብጽና ሱዳን ጋር ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት ያላት ቢሆንም፥ በፈረንጆቹ 2015 በካርቱም በሶስቱ ሃገራት መሪዎች የተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት መሰረት የግድቡ የውሃ አሞላል የግንባታው አካል መሆኑን እንደሚገልፅ አስረድተዋል።

የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተም አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በዋናነት በመንግስት በኩል እየቀረበ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላት ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ ተቋም ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር የጋራ ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም አንዳንድ አካላት በክልሉ ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ ገንቢ ሚና ከመጫወት ይልቅ ከእውነት የራቁ እና የተጋነኑ መረጃዎችን በማቅረብ በመንግስት ላይ ያልተገባ ጫና በማድረግ ላይ መጠመዳቸውን አንስተዋል።

ኬንያ እና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ሰላማዊ ግንኙነት ያላቸው ጎረቤት ሃገራት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ሃገራቱ ድንበር ብቻ ሳይሆን ህዝብም እንደሚጋሩ እና በተለያዩ መስኮች የሚደረጉ ትብብሮች ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ምቹ ሁኔታ አስረድተዋል።

በሃገራቱ መካከል በርካታ ስምምነቶች መፈረማቸውም የግንኙነቱን ጥልቀት አመላካች መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመው፥ ስምምነቶቹ ያሉበትን ደረጃ በመለየት ተግባራዊታቸውን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ተጨማሪ የትብብር መስኮችን መጨመር እንደሚያስፈለግ አፅንዖት ሰጥተዋል።

የሁለቱ ሃገራት የጋራ የከፍተኛ ኮሚቴ፣ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ እንዲሁም የጋራ የድንበር ኮሚቴ ስብሰባዎችን በሁለቱ ወገን በኩል አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ማካሄድ እንደሚያስፈልግም አውስተዋል።

አምባሳደር ሪሼል ኦማሞ በበኩላቸው፥ ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፥ ሃገራቸው ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ መሰረት ጉዳዮች እልባት ማግኘት እንዳለባች የምታምን መሆኗን ገልፀዋል።

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያና ኬንያ ባላቸው ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት የተፈራረሟቸውን በርካታ ስምምነቶች ተግባራዊነት በማፋጠን ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈለግ ጠቅሰው፥ በኮቪድ 19 ወረርሸኝ ምክንያት የጋራ ስብሰባዎች ሳይካሄዱ በመቆየታቸው የከፍተኛ የጋራ ኮሚቴ፣ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ እንዲሁም የጋራ የድንበር ኮሚቴ ስብሰባዎችን በማካሄድ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምክር እንዲሚያስፈልግም አንስተዋል።

የጋራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ማካሄድ እንዲሁም በሁለቱ ሃገራት የንግድ ምክር ቤቶች መካከል የጋራ የቢዝነስ ምክር ቤት ለማቋቋም የሚረዳውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አውስተዋል።

የሞያሌ የአንድ መስኮት ኬላ አገልግሎት በሃገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳለጥ እንዲሁም ህገ ወጥ የንግድ አካሄዶችን ለመግታት ካለው ጠቀሜታ አንፃር ወደ ስራ ማስገባቱ ያለውን አስፈላጊነት መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.