Fana: At a Speed of Life!

በችግር ውስጥ ያሉ አፍሪካውያንን ህይወት የሚያሻሻል የ1ነጥብ3 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በችግር ውስጥ ያሉ አፍሪካውያንን ህይወት የሚያሻሻል የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ስምምነት ማስተርካርድ ፋውንዴሽ እና የአፍሪካ በሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ በሚሊየን ለሚቆጠሩ አፍሪካውያንን የኑሮ ደረጃን ማሻሻል እና የተጎዳውን የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት በፍጥነት ከችግር እንዲላቀቅ የሚያስችል ነው፡፡

በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የሚተገበር የትብብር ስምምነት እንደሆነ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የአፍሪካን ምጣኔ ሀብት በፍጥነት ከችግር እንዲወጣ ማገዝ ዓላማ ያደረገ ስምምነት መሆኑን እና በጤናው ዘርፍ ላሉ ወጣት አፍሪካውያን አዳዲስ የስራ ዕድሎችንም ይፈጥራል ብለዋል የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪታ ሮይ፡፡

የተፈረመው አዲሱ አጋርነት በዓለም አቀፉ የኮቪድ 19 ክትባት ልማት (ኮቫክስ)፣ የአፍሪካ የኮቪድ 19 ክትባት ፍለጋ ቡድን(AVATT) እና በዓለም ዙሪያ ለአፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ የሚሰሩ አካላትን የእስከዛሬ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል ስምምነት ነው ተብሏል፡፡

ሁሉን-ዓቀፍ ተደራሽነት ያለው የክትባት ስርጭት ሥርዓትን ማረጋገጥ እና አፍሪካ የራሷን ክትባት እንድታመርት አቅሟን ማሳደግ ለአፍሪካ መልካም ሥራ ብቻ ሳይሆን ከወርርሽኙ ለመውጣትና የወደፊቱን የጤና ዋስትና ለማረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ ናቸው፡፡

‘‘የተደረገው ስምምነት በአፍሪካ አዲስ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ጉልህ እርምጃ ሲሆን፥ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ይህንን ታሪካዊ እንቅስቃሴ ቢቀላቀሉ በደስታ እንቀበላለን’’ ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.