Fana: At a Speed of Life!

የህንዱ አፍሪካብ ኩባንያ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህንድ አፍሪካብ ኩባንያ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል ከአፍሪካብ ኩባንያ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በበርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም መዋዕለ ንዋዩን ቢያሰፍ ተጠቃሚ እንደሚሆን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ በመንግስት ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዶክተር አክሊሉ፥ ኩባንያው በኢትዮጵያ ቢሰማራ በመንግስት በኩል አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግለትም አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካብ ኩባንያ የውጭ ግብይት ዳይሬክተር ዶክተር ሼክ ዩሱፋሊ ኢማኒ በበኩላቸው፥ ድርጅታቸው በአፍሪካ በታንዛኒያ፣ ኬንያ እና ዛምቢያ በማምረቻው፣ በግንባታ እና በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ተሰማርቶ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ለተለያዩ የኤሌክትሪክ መስመር አገልግሎት የሚውሉ ገመዶችን፣ ትራንስፎርመሮች እና ማብሪያና ማጥፊያዎችን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን እንደሚያመርትና በኢትዮጵያ በዘርፉ መሰማራት እንደሚፈልግም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.