የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኙነት ታሪካዊ፣ ጠንካራና በማናቸውም የውጭ ተፅዕኖ የማይናወጥ ነው- የጅቡቲው ፕሬዚደንት እስማዔል ዑመር ጉሌህ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማዔል ዑመር ጉሌህ ጋር ተወያየ።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የተመራና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ተመስገን ጥሩነህን ያካተተ የመንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ክቡር እስማዔል ኡመር ጌሌህ ጋር ተገናኝተው በወቅታዊ አካባቢያዊና በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ታሪካዊ፣ የማይለዋወጥና በማናቸውም የውጭ ኃይል ተፅዕኖ የማይናወጥ መሆኑ ተነስቷል።
የህዘብ ለህዝብ ትሥሥራቸውም በባህልና ቋንቋ ጭምር የተሳሰረና በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ለፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን÷ በመንግስት በኩል በአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቋቋም የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አብራርቷል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ ድጋፎችንም አጠናክሮ የማስቀጠልና መደበኛ የትምህርትና የግብርና ሥራዎችም እንዲጀመሩ የተደረገበት አግባብ መኖሩም ነው የተገለጸው፡፡
የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኡመር ጌሌህ በበኩላቸው÷በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ታሪካዊ፣ ጠንካራና በማናቸውም የውጭ ተፅዕኖ የማይናወጥ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ጅቡቲ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን ለመፍታት እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀው÷ የሁለቱ አገራት ትስስር ጠንካራ እንደሆነና መለያየት በማይችል መልኩ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአንዱ አገር ውስጥ የሚፈጠር ችግር ሌላውም ላይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር ፕሬዝዳንቱ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል ፡፡
በመሆኑም ትሥሥሩን ይበልጥ ለማጠናከር ጅቡቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኗን ለልዑካን ቡድኑ አረጋግጠዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከጅቡቲው አቻቸው ጄኔራል ዘካሪያ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብና የመንግስታቱ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አንስተው ይህንኑ ግንኙነት በወታደራዊ መስክም ማስቀጠል እንደሚገባ ተወያዮቹ አንስተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በወታደራዊ መስክ የመረጃ ልውውጥ፣ የትምህርትና ስልጠና ትብብር እንዲሁም የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በሁለቱ አገራት የጋራ ድንበርና የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደርን ሰላማዊ ቀጠና ከማድረግ አኳያም በትብብር እንደሚሠሩ የተወያዩ ሲሆን በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጋር ሁለትዮሽ ውይይቶችንም አጠናክረው ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጅቡቲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!