Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ከ2 ሚሊየን 764 ሺህ በላይ ምርመራዎች ተደርገዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኮቪድ19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ አንድ አመት ከ5 ወር ወዲህ ከ2 ሚሊየን 764 ሺህ በላይ ምርመራዎች መደረጋቸው ተገለፀ።

የጤና ሚኒስቴርና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት ትኩረቱን በኮቪድ19 ያደረገ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ የወረርሽኙ መከላከል ሂደትና ችግር ፈቺ ምርምሮች ከኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች ጥናቶችን ያቀርባሉ።

በእስካሁኑ ሂደት 3 ሺህ 329 የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ሲያዙ፣ 36 ያህሉ ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፥ 176 ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘው ህክምና በመከታተል ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

ጥንቃቄ ባልተደረገ መልኩ መሰባሰቦች እየሰፉ መምጣታቸው፣ አርዓያ መሆን የሚገባቸው አካላት ሀላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ለቫይረሱ መጨመር ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አስቻለው አባይነህ፥ ባለፉት ጊዜያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተሰሩ ስራዎች የኮቪድ19 ወረርሽኝ ያደርስ የነበረውን የከፋ ጉዳት መቀነስ የቻሉ ናቸው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎቻቸውን ከመረመሩ ሀገራት አንዷ መሆን እንደቻለች ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሰሯቸው ስራዎች አበረታች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ተቋማቱ በተለይም በጥናትና ምርምር ብሎም በችግር ፈቺ ፈጠራዎች የበሽታውን መከላከል ሂደት እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.