Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ሃገራት ይሰጡ የነበሩ ሕክምናዎችን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለመስጠት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የካንሰር እና ልብ ሕክምናን ጨምሮ በውጭ ሃገራት ብቻ ይሰጡ የነበሩ ሕክምናዎችን በሆስፒታሉ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ በዓመት ከ160 ሺህ በላይ ሰዎች በተለያዩ የካንሰር በሽታዎች እንደሚያዙ ተጠቁሟል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛኸኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመሩ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል በመንግስት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ለሆስፒታሉ ከመንግስት በተመደበ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የካንሰር፣ የልብና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና መስጫ ማዕከላት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ማዕከላቱ ከ40 በላይ የተመላላሽ ኬሞ ቴራፒ ሕክምና መስጫ ከፍሎች፣ 11 የቀዶ ሕክምና ክፍሎች፣ እንዲሁም አምስት የጨረር ሕክምና መስጫ ክፍሎች አላቸውም ነው ያሉት።

ማዕከላቱ ሥራ ሲጀምሩ የባለሙያ እጥረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት ዶክተር ወንድማገኝ፥ ለዚህም ባለሙያዎች በውጭና በሀገር ውስጥ እንዲሰለጥኑ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“በአሁኑ ወቅት ከ12 በላይ የካንሰር ህክምና ባለሙያዎች በቅዱስ ጳውሎስና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገ ሲሆን የማዕከላቱ ግንባታ ሲጠናቀቅም ወደ ሆስፒታሉ እንዲዛወሩ ይደረጋል” ብለዋል።

በጳውሎስ ሆስፒታል ከሚገነቡት ማዕከላት በተጨማሪ ጎንደር፣ ሃዋሳ፣ ሐረር ጅማ እና መቐለን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ የካንሰር ማዕከላት ህብረተሰቡን ከእንግልትና ከወጪ እንደሚታደጉ ታምኖባቸዋል።

በተጨማሪም ማዕከላቱ በሃገሪቱ የህክምና ቱሪዝምን በማስፋፋት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል።

የሦስቱ ማዕከላት ግንባታ በአሁኑ ወቅት 67 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ የግንባታ ሥራውን በቀጣዩ ዓመት መጨረሻ ድረስ ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ህክምናውን ለማስጀመር ይሰራል ነው የተባለው፡፡

የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው የዘርፉ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ከ18 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ካንሰርና የልብ ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩ መዘገቡ ይታወሳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.