Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የ10 ወራት የሥራ አፈጻጸም ተገመገመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የ10 ወራት የሥራ አፈጻጸም ተገመገመ፡፡
በግምገማው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይን ጨምሮ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ10 ወራት የሥራ አፈጻጸም፣ ድክመትና ጥንካሬው ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በክልሉ የሰቆጣ ቃል ኪዳን በጀት አጠቃቀም 92 በመቶ መሆኑን ገልጸው አፈጻጸሙ ተዓማኒ እንዲሆን በፋይናንስ ሥርዓቱ መሰረት ማወራረድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህም የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ተጠናክረውና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መሥራት አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዘርፎቹ እስካሁን በሰቆጣ ቃል ኪዳን በጀት ያከናወኗቸውን ዝርዝር ሥራዎች ለፌዴራል መንግሥት እንዲያቀርቡና በቀሪ ወራቶችም የሚሰሩ ተግባሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በተለመደው መልኩ ተግባራቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ2014 በጀት ዓመት ዝርዝር እቅድ እንዲዘጋጅ አቅጣጫ መስጠታቸውን ታውቋል፡፡
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም በእናቶችና ህጻናት አመጋገብ ዙሪያ እውቀት እና አመለካከትን ለማሻሻል የሚያስችሉ እንዲሁም ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ ሥራዎች የሚከናወኑበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.