Fana: At a Speed of Life!

በ15 ሚሊየን ብር በድል ይብዛ ከተማ ለሚገነባው ትምህርት ቤት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 5 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በድልይብዛ ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት በዳሸን ባንክ እና በአማራ ልማት ማህበር በጋራ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩን የአማራ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ እና የዳሽን ባንክ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይህአለም አቅናው በጋራ በመሆን አስቀምጠውታል።

የአልማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ በዚህ ወቅት እንዳሉት የክልሉን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ አልማ በትኩረት እየሰራ ነው።

በክልሉ የጥራት ደረጃ የሚያሟሉ ትምህርት ቤቶች ድርሻ 16 በመቶ ነው ያሉት አቶ መላኩ የራስን ችግር በራስ ለመፍታት በሚለው መርህ ስራዎች በተጠናከረ መንገድ እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የዳሽን ባንክ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይህአለም በበኩላቸው ባንኩ ከመደበኛ የተቋሙ ተልዕኮ ውጪ በተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፈ ለውጥ አስመዝግቧል አሁንም ይቀጥላል ነው ያሉት።

በድል ይብዛ ከተማ የሚገነባው የትምህርት ቤት ግንባታ ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው በዳሽን ባንክ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው ለመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ 15 ሚሊየን ብር እንደተመደበለት ገልጸዋል።

ግንባታው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል የተባለ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጅ የሚያድግ በመሆኑ 51 ሚሊየን ብር በጀት ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለአለም ፈንታሁን በዞን ደረጃ 96 በመቶ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶቸን ደረጃ እና ጥራት ለማሳደግ የአማራ ልማት ማህበር እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉት አስተዳዳሪው ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የወረዳው አስተዳደሩ ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ሰባት ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱ ታውቋል።

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.