Fana: At a Speed of Life!

የለውጥ ሂደቱ  በስኬት እንዲጠናቀቅ  ሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የለውጥ ሂደቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡

ዳያስፖራ ኤጀንሲና በኢፌዴሪ ሚሲዮኖች አስተባባሪነት በመላው ዓለም ከሚገኙ የዳያስፖራ ወጣት ተወካዮች ጋር በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የመከረና በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ  አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ በሆነ ለውጥ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ይህ የለውጥ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ ከያቅጣጫው ፈተና ቢበዛባትም በጽናት ወደፊት በመራመድ ላይ እንዳለች ጠቅሰው÷ ፈተናዎቹ የህዝቡን አንድነት ይበልጥ እያጠናከሩት መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የፈተኛዎቹ መብዛት ኢትዮጵያ ሁሉንም አቅሞቿን አስተባብራ እንድትጠቀም የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው÷ይህ ትውልድም እንደቀደምት አባቶቹ ታሪክ ሰሪነቱን የሚያሳይበት ወቅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም ወቅቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚኖራቸውን ነጻና ሁሉን አሳታፊ ምርጫን እንዲሁም ሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት የሚከናወንበት መሆኑን አስታውሰዋል።

ከዚህ አንጻር በሃገራችን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመቋቋም የዳያስፖራ ወጣቶች የሚያከናውኑት የተደራጀና ፈጣን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በስኬት መሻገር እንዲቻል ሚሲዮኖችና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ፈተናውን የሚመጥን ጥረት ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።

ወጣቱም የተናበበ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ሊያከናውን እንዲሁም ሁሉም አካላት በቃላቸው መሰረት ለመገኘት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው÷ ዳያስፖራው ለሃገሩ አለኝታ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችንና ጥሪዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት አሰባስቦ እየላከ በመሆኑ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍም ዳያስፖራው የኢትዮያን ገጽታ ለማጠልሸትና ያልተገባ ጫና ለማሳደር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመቃወም ታላላቅ የተቃውሞ ሰልፎችን፣ የትዊተር ዘመቻዎችንና የማግባባት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የዳያስፖራው አንድ ክፍል የሆነውን ወጣት ዳያስፖራ በማሳተፍ የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ በፓናሊስትነት የቀረቡ አምባሳደሮችም በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመከላከል በሚያስተባብሯቸው ሚሲዮኖች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስረድተዋል።

በመድረኩ ላይ ከ400 በላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችን የወከሉ አምባሳደሮች፣ የሚሲዮን መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የወጣቶች ዳያስፖራ ተወካዮች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.