Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፌዴራልና ከክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት የተውጣጣው ከፍተኛ አመራሮችና አባላት በሀገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በመምከር የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡

የፌዴራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ንቁ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ እንዲሁም የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይስተጓጎል በብቃት እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የህዝብ ሰላምና የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናኑንም ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ገልጿል።

ምርጫው መንግሥት የሚመሠረትበት ህጋዊ ሂደት በመሆኑ ሁሉም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከፌዴራልና ከክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሃላፊነቱም እንደሚወጣም ነው ያስታወቀው፡፡

በተጨማሪም ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና የላቀ የህዝብ ተሳትፎና ተቀባይነት እንዳይኖረውና የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎች ፍላጎታቸው እንዳይሳካ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የሰላም አጠባበቅ መርህ በመተግበር ደህንነቱን ለማረጋገጥ ይሰራልም ነው ያለው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ዘገባ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ እንዲዘግቡና ከተገቢው ሙያዊ አዘጋገብ የሚያፈነግጡ መገናኛ ብዙሃን ሲያጋጥሙ ፈጣን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ግዴታውን እንደሚወጣም ነው ያስታወቀው፡፡

ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የሃሰት መረጃዎችን፣ ጥላቻዎችንና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎችም መንገዶች የሚያስተላልፉና የሚያሠራጩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሽብር ቡድኖች እንዲሁም የትኛውም አካላት ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ በህግ የሚጠየቁበት አሰራር በመዘርጋቱ ለተግባራዊነቱ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብሏል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ፣ ተዓማኒና በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የፌዴራልና የክልል የፀጥታና ደህንነት አባላት ፍጹም ገለልተኛና ሙያዊ በሆነ መንገድ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉም ብሏል በላከው መግለጫ፡፡

ህብረተሰቡ ምርጫው ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት በመደረጉ በዕለቱ በነቂስ በመውጣት የፈለገውን እንዲመርጥ እንዲሁም ከምርጫው ሂደቶች ጋር በተያያዘ የደህንነት ስጋት የሚፈጥሩ አዝማሚያዎች ሲያጋጥሙት የሚሰጠው የተለመደ ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.