Fana: At a Speed of Life!

ኳታር ሶስቱ የተፋሰሱ አገራት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመክሩ ታበረታታለች- የኳታር የማኒሲፓሊቲ እና አካባቢ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ ከኳታር የማኒሲፓሊቲ እና የአካባቢ ሚኒስትር ዶክተር አብደላህ ቢን አብዱላዚዝ አልሱቤይ ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ሳሚያ የሕዳሴ ግድብ ድርድርን፣ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን እና በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለሚኒስትሩ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
በውይይቱም አምባሳደር ሳሚያ ኢትዮጵያ ከኳታር ብሎም ከዓረቡ አለም ጋር ያላትን ታሪካዊ ትስስር በማውሳት÷ ይኸው የቆየ ጠንካራ ግንኙነት ወደላቀ የትብብር ምዕራፍ እንዲሸጋገር የምትሻ መሆኗን አስረድተዋል።
ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋና መሰረት መሆኑን፣ ሰፊ የመሬት፣ የሰው ኃይል እንዲሁም የውሃ ሃብት ያላት አገር መሆኗን አንስተዋል።
በመሆኑም የግብርና ዘርፉ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አምባሳደር ሳሚያ ጠቁመዋል።
በዘርፉ ለሚደረጉ ሁለገብ ትብብሮች መሰረት እንዲሆንም በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የግብርና፣ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ስምምነት በአፋጣኝ እንዲፈረም በውይይቱ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ከዚህ በተጨማሪም ኳታር የምግብ ዋስትና ፕሮግራሟን እውን ለማድረግ ከፍተኛ የግብርና ኢንቨስትመንት አማራጭ ካላት ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ልትሰራ እንደሚገባ አምባሳደሯ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ቴምርን ለማምረት ከኳታር የተሞክሮ ልውውጥ፣ የችግኝ አቅርቦት እና የቴክኒክ ድጋፍ ማግኘት የሚቻልበት እድል እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘም፣ ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ ዘመቻዎችን እያካሄዱ የሚገኙ በመሆናቸው፣ በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
የኳታር መንግስት “Plant Million Tree” የሚል ዘመቻ እያደረገ ሲሆን÷ በኢትዮጵያም ሰፊ የአረንጓዴ ልማት ስራ እየተሰራ ይገኛል ይህንን ጥረትም ሚኒስትሩ አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም በኳታር በሚካሄደው ሆርቲካልቸር ኤክስፖ 2023ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ግብዣ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ በዶሃ እየተካሄደ ካለው የዓረብ ሊግ የምክክር ስብሰባ ጋር አያይዘው ባነሱት ሃሳብ “የሕዳሴ ግድብ ድርድር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።
ኳታር ሶስቱ የተፋሰሱ አገራት የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመክሩ ታበረታታለች ነው ያሉት ።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.