Fana: At a Speed of Life!

የብሪታኒያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካልና የህከምና መሳሪያዎች ኢንቨስትመንት ዙሪያ እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በአፍሪካ አድቫይዘሪ ፓርትነር አዘጋጅነት “የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ” በሚል በለንደን በውይይት ተደረገ፡፡
በውይይቱ የብሪታንያ የውጪ ጉዳይና የአለምአቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት የስራ ሃላፊዎችና ባለሃብቶች ፣ በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የአለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር ፣የጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ መልእክተኛ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት አሰተዳደር ፣የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ምርቶች አምራቾች ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ፋርማሲዩቲካልና የህከምና መሳሪያዎች ኢንቨስትመንት በ10 አመቱ የመንግስት የልማት እቅድ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ መሆኑን ገልፀው ፣ ዘርፉ በየአመቱ በአማካይ ከ15 በመቶ በላይ እድገት እያሳየ በመሆኑ ለኢንቨስተመንት ከፍተኛ ተመራጭነት አለው ብለዋል ፡፡
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ልዩ የንግድ መልእክተኛ ሎርድ ባቴስ በበኩላቸው አገራቸው ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ተከትሎ ገለልተኛ የሆነ አለም አቀፍ የንግድ መርሆዎችን ለመከተል በተዘረጋው አዲስ ፖሊሲ አንዱና ዋናው ትኩረታቸው የአፍሪካ ሀገሮች መሆናቸውን ገልፀው ኢትዮጵያ ዋናዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በወጪ ንግድ ላይ ለሚሰማሩ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች ከ 2 ቢሊየን ፓውንድ በላይ የገንዘብ ድጋፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታደስ እንደተናገሩት የፋርማሲዩቲካልና የህከምና መሳሪያዎች 88 በመቶው ከውጪ የሚገቡ በመሆናቸው ይህን ለማስቀረትና በሀገር ውስጥ ለማምረት ሰፋፊ እና አጓጊ የኢንቨስትመንት ምቹ ና አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልፀዋል ፡፡
የአፍሪካ አድቫይዘሪ ፓርትነር ዳይሬክተር ክርስቶፈር ሞሪስም እንዲሁ ብሪታንያ በህክምና መሳሪያዎች እና በፋርማሲቲዩካል ምርምርና ቴክኖሎጂ እውቀት የዳበረ ልምድ እና አቅም ያላት በመሆኑ ከአውሮፓ መውጣቷን ተከትሎ ያለው የኢንቨስትመንት እድል በአፍሪካ መሆኑን አመልክተው ኢትዮጵያ ለዚህ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረች በመሆኑ ባለሃብቱ እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አቶ በየነ ገብረመስቀል በበኩላቸው ኤምባሲው የብሪታንያ ለሃብቶች በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ኢንቨስትመንት እና ንግድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ከሚመለከታቸው ጋር ለማገናኘት ዝግጁ እንደሆነና በቀጣይም ባለሃብቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.