Fana: At a Speed of Life!

በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዙርያ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ውሎች ተቀባይነት የላቸውም- በኬንያ የኡጋንዳ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም ኬንያ ከሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደሩ በኬንያ ከስዊዛርላንድ አምባሳደር  ቫሌንቲን ዜልዌጌር፣ ከአዲሱ የኡጋንዳ አምባሳደር ዶክተር ሀሰን ዋስዋ እንዲሁም ከቤላሩስ አምባሳደር  ፔቫል ቪዚየትኪን ጋር ነው የተወያዩት።

በውይይትም  የህዳሴ ግድብ ድርድርን ጨምሮ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

በወቅቱም  የኡጋንዳው አምባሳደር ዶክተር ዋስዋ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ÷ መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ተመኝተዋል።

አያይዘውም  አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዳላት የገለፁት  ጠቁመው÷ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዙርያ የተደረጉ የቅኝ ግዛት ውሎች ተቀባይነት እንደሌላቸው እንዲሁም ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር በትብብር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዜልዌጌር ስዊዛርላንድ የላይኛው ተፋሰስ አገር መሆኗን እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም እና አስተዳዳር ላይ ከፍተኛ ልምድ እንዳላት ተናግረዋል።

ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች የትብብር እንጂ የግጭት መንስዔ መሆን እንደሌለባቸውም አምባሳደሩ ገልፀዋል።

ተቀማጭነታቸውን ኬንያ አድርገው በኢትዮጵያ የተወከሉት የቤላሩስ አምባሳደር ፔቫል ቪዚየትኪን በቅርቡ ለ ኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደሩ በዛሬው  ዕለት በኬንያ የኢትዮጵያን ኤምባሲ የጎበኙ ሲሆን ÷ከአምባሳደር መለስ ዓለም ጋር በሁለቱ አገሮች ወዳጅነት እና ትብብር ዙርያ ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደር ቪዚየትኪን የቤላሩስ መንግስት ኢትዮጵያን በመወከል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራልነት ቦታ ለሚወዳደሩት ለዶክተር አርከበ ዕቑባይ ድጋፍ እንደሚሰጥ መግለጻቸውን ኬንያ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.