Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶች በንቃት አካባቢያቸውን መጠበቅ አለባቸው – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶች በንቃት አካባቢያቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የባሕር ዳር ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ የመዝጊያ መርኃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፥ ባለፉት ጊዜያት ልዩ ልዩ ችግሮች ቢያጋጥሙም የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ይህንን ያሉት በፓርቲው ደጋፊዎች በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ ሥራዎችን ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መሆኑን የዘገበው አሚኮ ነው፡፡

የልማት ሥራው እንዲቀጥልም የሕዝቡ ድጋፍ፣ የመሪዎች በሳል አመራር እና የክልሉ መንግሥት እገዛ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፥ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ በአንድነት መሥራት ያስፈልጋል ያሉት የፓርቲው ደጋፊዎች በተለይ በድኅረ ምርጫው የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር መዘናጋት አይገባም ብለዋል፡፡

የሕዳሴ ግድቡን መጠናቀቅ የማይሹ አካላት የሚፈጥሩትን ጫና በመመከት ግድቡን ማጠናቀቅ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ መንግሥትና ሕዝብ በሰላም ጉዳይ ላይ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በግፊትም ሆነ በስሜት ሰላም ለማደፍረስ የሚሰማሩ አካላትን ከመምከር ጀምሮ እየተከታተሉ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር፥ በከተማዋ የሚነሳ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን ከተማዋን ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝምና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የሕዝብ መፈናቀልን ለማስቆም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳድሩ፥ የተፈናቀሉትን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ መፈናቀልን ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀሙ አካላትን መታገል እንደሚገባም አሳስበው ወጣቶች አካባቢያቸውን በንቃትእንዲጠብቁ ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.