Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል 19 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ከፍ ብሏል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታውቋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንደገለጹት በክልሉ በባለፈው አመት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ከተተከሉት 84.33 በመቶ የሚሆነው መፅደቅ ችሏል።

በ3 ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ቡዙ ጥቅም ያላቸው 1 ነጥብ 31 ቢሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ፍቃዱ በበልግ ወቅት 254 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባልደረባ ነግረውታል።

ለጎረቤት ሀገር የሚሰጡ 25 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል ነው የተባለው።

ባለፉት 3 አመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ያለው የደን ሽፋን እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከቱን የክልሉ አካባቢ ጥበቃ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ እንደገለፁት በክልሉ በ2007 ዓ.ም 19 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ወደ 23 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን ባለፉት 3 ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአዳዲስ መሬቶች በችግኝ መሸፈናቸው ለደን ሽፋኑ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልል ደረጃ በቤንች ሸኮ ዞን ሰኔ 10 በይፋ ይጀመራል።

በተስፋዬ ምሬሳ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.