Fana: At a Speed of Life!

የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም የዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አማካኝነት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ችግር ለመፍታት እንዲቻል የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም የተጠናውን የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት የዘርፉ አስፈጻሚዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው  ዛሬ ውይይት የተካሄደው።

መድረኩን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገ/መስቀል ጫላ ÷የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሃገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በመታመኑ ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂና ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

የኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ፣ የገበያ እና የፋይናንስ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ከፍተኛ የመነሻና የማስፋፊያ የካፒታል እጥረት መኖር አንዱ የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም  የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለማስፋፋት የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በፋይናንስ ድጋፍ ለመቅረፍ፤ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ባንክ ለማቋቋም የፍላጎት ዳሠሣ ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።

ባንኩን ለማቋቋም በተዘጋጀው የፍላጎት ዳሰሳ ረቂቅ ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃዎችንና አስተያየቶችን በመሰብሰብ ሠነዱን በማዳበር፤ በቀጣይ ባንኩ ስለሚቋቋምበት የአዋጭነት ጥናትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ መድረኩ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ  ገልጸዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የተከበሩ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የስራ ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር÷ የቀረበው ጥናት ከመንግስታዊ ድጋፎች አንዱ የሆነውን የፋይናንስ አቅርቦትን የተመለከተ ነው ማለታቸውን ከከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.