Fana: At a Speed of Life!

ታሪካዊዉን ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ታሪካዊዉን ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በክልሉ እና በሀገር ሀቀፍ ደረጃ የሚደረገውን ምርጫ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል  እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊ፣ተአማኒ እንዲሁም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የህዝቡ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የግል እጩ ተመራጮች፣የምርጫ አስፈጻሚዎች እና የመንግስት ሚና ወሳኝ ነው ብሏል።

ከሁሉም በላይ ሰላም ለሁሉም እንቅስቃሴ መሰረት በመሆኑ፣መንግስት ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት በማቀናጀት፣የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ በቂ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተጨባጭ ስራ ገብቷልም ነው ያለው በመግለጫው፡፡

ምርጫው በሚደረግበት አካባቢ ሁሉ ለምርጫው ስኬት የሚሰሩ አካላት ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ  እንዲሁም ዜጎች ያለ አንዳች ስጋት ወጥተው እንዲመርጡ መንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ይወጣል ብሏል፡፡

በዚህም በተለይ የክልል እና የፌደራል የጸጥታ አካላትን በጋራ በማቀናጀት በሁሉም አካባቢዎች አሰማርቷል ነው ያለው፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን  መመሪያዎች እና ደንቦችን ማዕከል በማድረግ የተሰጠውን ሀላፊነት በሙሉ በታማኝነት  በመወጣት ላይ ይገኛልም ብሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በምርጫው ዋዜማ፣በእለቱ እና በድህረ ምርጫ ወቅቶች የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ለማድረግ  ለሚመለከታቸው አካላት ተልኮ ከመስጠት ባለፈ፣ ከሰፊው ህዝብ ጋር ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯልም ነው ያለው፡፡

ስለዚህ ሰፊው ህዝብ፣ ሶስት ትላልቅ ሀላፊነቶችን ወስዷል፡-

የመጀመሪያው ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ በሰላም  እንዲጠናቀቅ፣ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የምርጫውን ሰላማዊነት ለማወክ የሚደረግ የትኛውንም ሙከራ እንዲያጋልጥ ፡፡

ሁለተኛ ያለምንም ስጋት የምርጫ ካርድ እንደወሰደ ሁሉ፣ ያለምንም ስጋት እና ፍርሀት ይሆነኛል የሚለውን የሚፈልገውን እጩ  በነጻነት እንዲመርጥ ይጠበቃል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የምርጫው ውጤት በህግ አግባብ በተሰጠው አካል እስኪገለጽ፣ ተረጋግቶ እና ለየትኛውም ውዥንብር ጆሮ ሳይሰጥ ደምጽን ማስከበር አለበት ብሏል፡፡

በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት የጸጥታ መዋቀር 6ኛውን ምርጫ ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊ፣ተአማኒ እና ፍትአዊ ለማድረግ መወጣት የሚገባውን ሃላፊነት በተመለከተ የግንዛቤ ስራዎች ተሰርተዋልም ነው ያለው፡፡

በመሆኑም ከየትኛው ጊዜ በበለጠ የተያዙትን ግቦች በሙሉ ለማሳካት አቋም ይዟል ብሏል፡፡

በተለይ የክልል እና የፌደራል የጸጥታው አካልት፤ የጥፋት ሀይሎቸን ሴራ ለማክሸፍ ጠንክሮ እየሰሩ ይገኛሉም ነው ያለው፡፡

በህግ መንግስት የተረጋገጠውን የህዝቦችን ነጻነት እና ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን ለመጠበቅ የክልሉ መንግስት ዝግጁ  ነው ሲል በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ህዝቡም በሰላም ወጥቶ የሚፈልገውን መንግስት መምረጥ እንዲችል የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት አደራ ወስደዋልም ነው ያለው፡፡

ከምንም በላይ የመጀመሪያው የምርጫ ምዕራፍ ውስጥ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶች ያሳዩትን መልካም ስነ-ምግባር  መንግስት ያለውን አድናቆት እና ምስጋና ይገልጻልም ነው ያለው።

በቀጣይ ጊዜያት የክልላችንን እና የሀገራችንን ሰላም በመጠበቅ ምርጫው በተሟለ መልኩ እንዲሳካ፣ የበኩላችሁን ተሳትፎ እንድታደርጉ አደራ እንላለን፡፡

በመጨረሻም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከአባቶቻችን በወረስነው የሀገርን ክብር እና ለአላዊነት በመጠበቅ አዲስ ታሪክ እንድናስመዘግብ ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ጥሪ በማቅረብ፣ መንግስት የምርጫውን ሰላማዊነት አስተማማኝ ለማድረግ ሰፊ  ዝግጅት እንዳለው ያስታውቃል ብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.