Fana: At a Speed of Life!

በምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ለማቅናት የነበረውን ተስፋና እልህ በግልፅ ያየንበት ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ከሚል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ለማቅናት የነበረውን ተስፋና እልህ በግልፅ ያየንበት ነው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ከሚል ገለጹ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከዋዜማው ጀምሮ የነበረውን ሂደት ገምግሟል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ በቴክኖሎጅ የታገዘ የመረጃ ልውውጥ ሲያደርግ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን፥ ከክልሎች ጋር በተሰራው የጋራ ስራ ከተወሰኑ ቦታዎች ውጭ ምርጫው በሰላም እንዲከናወን መደረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት፥ በምርጫ ሂደት ውስጥ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት የነበራቸው ትስስርና ፈጣን ምላሽ የፖሊስ አካላትን ገለልተኛ ለማድረግ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በምርጫ ሂደቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ለማቅናት የነበራቸውን ተስፋና እልህ በግልፅ ያየንበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ ምርጫው በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ችግኝ የተተከለበት፣ ጠላቶች እንደተመኙት ሳይሆን ህዝባችን እንደፈለገው ሆኖ እየቀጠለ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የህግ የበላይነት ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባበው በበኩላቸው፥ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ የስጋት ቀጠናዎች ተለይተው ሰፊ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

‘‘ከክልሎች ጋር የነበረው ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እና ግብረ መልስ የሚያኮራ ነው’’ ማለታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡

በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ያሉ ኢንቨስተሮችን በቅርበት በመከታተል ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት እንዳያድርባቸው ሰፊ ስራ ተሰርቷል ያሉት ወይዘሮ ፍሬዓለም፥ የህዝቡ ጨዋነትና የህግ አስከባሪ ሃይሎች የነቃ ተሳትፎ ምርጫው በሰላም እንዲሄድ አድርጓል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.