Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮልን አጸደቀች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ  የሰዎች እና ህዝቦች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮልን ተቀብላ አጸደቀች።

ፕሮቶኮሉ በአፍሪካ የሚገኙ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ አረጋውያንን ፍላጎት በተመለከተ በልዩነት ትኩረት ሰጥቶ ለመተግበር የሚያስችል መብቶቻቸውን እና ሊደረግላቸው የሚገባ ጥበቃን፣ አስመልክቶ አባል ሀገራት ሊወስዱት የሚገባቸውን ዕርምጃዎች አብሮ የያዘ  ነው፡፡

በዋናነትም በማህበረሰብ፣ በባህል ከተቀመጡ አስተሳሰቦች ጨምሮ ከማንኛውም መድልኦ ነጻ  የመሆን መብት፣ ዕኩል የፍትህ እና የህግ ጥበቃ የማግኘት መብት፣ የራሳቸውን ደህንነት አስመልክቶ ካለማንም ጣልቃ ገብነት  ውሳኔ የመወሰን፣ የጤና፣ የአካል፣ የልምድ፣ አቅማቸውን ያማከለ የስራ ዕድል ማግኘት መብት፣ ማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ መብት፣ ድጋፍና እንክብካቤ ማግኘት መብት፣ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች፣ በባህል በመዝናኛ እና በስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ የመሳተፍ መብቶችን የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም በልዩ ሁኔታ ለሴት አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑ አረጋውያን እና በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አረጋውያንን አስመልክቶ የተለያዩ ልዩ ልዩ ጥበቃዎችን  የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎች ማካተቱን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያም የአፍሪካ ህዝቦች እና ሰዎች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮልን በአዋጅ ቁጥር 1182/2012 በማጽደቅ የማስፈጸም ሀላፊነቱን ለሰራተኛ እና ማሀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በመስጠት የሀገሪቱ ህግ አካል አድርጋለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.