Fana: At a Speed of Life!

የህወሃት አሸባሪ ቡድን ቦታዎችን የተቆጣጠረ በማስመሰል ያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ የሃሰት ነው – መከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ለ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሰላምና ጸጥታ ሲባል በአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫ የሰራዊቱን መሰመራት ተከትሎ የአሸባሪው ርዝራዥ ታጣቂ ቡድን ቦታዎችን የተቆጣጠረ በማስመሰል ያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ የሃሰት መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሃገር አቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ የሃገር ውስጥና የውጭ ስጋትን ለመመከት እንዲቻል ከትግራይ ክልል ወደ አራቱም አቅጣጫ የሰራዊት ስምሪት መደረጉንም አሳውቋል።

የመከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ፥ የህወሃት ታጣቂ ቡድን ይህንን እድል በመጠቀም ከተደበቀበት ልዩ ልዩ ቦታና ሁኔታ በመውጣት ቦታዎችን የተቆጣጠረ በማስመስል የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ማሰራጨቱን ገልጸዋል።

ርዝራዥ ሃይሉ ይህን እያደረገ ያለውም አለም አቀፍ ትኩረት ለመሳብና ከመንግስት ጋር አደራድሩኝ ለማለት እንዲሁም አጀንዳ ለማስቀየር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሰሞኑን በትግራይ ክልል ተፈጸመ ስለተባለ የአየር ጥቃት ማብራሪያ የሰጡት ኮሎኔሉ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ባገኘው ጥብቅ መረጃ ውጤታማ ኦፕሬሽን መፈጸሙን ገልጸዋል።

ኦፕሬሽኑ የሰመዓታትን በአል ለማክበር በሚል የተዘጋጀን የአሸባሪውን ሃይል ለይቶ የመታ ነበርም ብለዋል።

በገበያ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል ለሚል ሃሳብ ምላሽ ሲሰጡም የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ከገበያ ሰአት ውጪ ከ9 ሰዓት በኋላ የተደረገ ኦፕሬሽን ነበርም ብለዋል።

በዚህም ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

በሃሰት ፕሮፖጋንዳ የትግራይ ወጣትን እየደለለ የሚገኘውን የጁንታውን ሃይል ሴራ ተረድቶ የክልሉ ነዋሪ ራሱን በመልሶ ማቋቋም ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ መላው ህብረተሰብም ይህንን እንዲረዳ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተስፋዬ ከበደ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.