Fana: At a Speed of Life!

በክረምቱ በትምህርት ዘርፍ 25 ቢሊየን ብር የሚገመት የዜግነት አገልግሎት ይከናወናል – ዶክተር ቶላ በሪሶ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ ወቅት በትምህርት ዘርፍ 25 ቢሊየን ብር የሚገመት የዜግነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማከናወን ታቅዶ ወደ ተግባራዊ ስራ መገባቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ አስታወቁ።
ዶክተር ቶላ በሪሶ በሰጡት መግለጫ÷ እኛ ትንሽ ሰርተን ካሳየን ህዝብ የበለጠ መስራት እንደሚችል ከአምናው ተሞክሮ ወስደናል ብለዋል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት መምህራን፣ ተማሪዎችንና ህዝቡን በሰፊው በማሳተፍ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን አንስተዋል፡፡
ጨፌው ባለፈው ዓመት ባጸደቀው የዜግነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አዋጅ መሰረት በማድረግ በወቅቱ የ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከ34 ሺህ በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባቱን÷ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን መጻህፍትን መሰብሰቡንና ሌሎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸው በመግለጫው ተነስቷል፡፡
እንደ ዶክተር ቶላ መግለጫ ÷በተያዘው የክረምት ወቅት ከመግቢያው ጀምሮ 25 ቢሊየን ብር የሚገመት ወደ 11 ዓይነት የስራ ዘርፎችን ለማከናወን በማቀድ ወደ ተግባራዊ ስራ ተገብቷል።
ከስራ ዘርፎቹም መካከል 3 ሺህ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ፣ 3 ሚሊየን መጻህፍትን መሰብሰብ ፣ወደ 3 ሚሊዮን ጎልማሶችን ማስተማር እና በክልሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ወደ 15 ሺህ የመምህራን ቤቶችን መስራት የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል፡፡
ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን መገንባት ፣ያረጁ ክፍሎችን ማደስ፣ የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆችን መደገፍና ትምህርት ቤቶችን አረንጓዴ ማልበስም ሌሎች የሚሰሩ ተግባራት እንደሆኑ በመግለጫው ቀርቧል፡፡
በዘርፉ ትንሽ ሰርቶ በማሳየቱ የበለጠ መስራት የሚችል ህዝብ እንዳለ መገንዘብ ችለናል ያሉት ዶክተር ቶላ በሪሶ÷ በዚህም ባለፈው በጉልበቱ ፣ ክህሎቱ እና ገንዘቡ ሰርቶ ላሳየው ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።
አሁንም ተማሪዎች መምህራንና ሌላም ህብረተሰብ እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሙሉ አቅማቸው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.