Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የቡና ልማት ለማገዝ 42 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የቡና ልማት ለማገዝ 42 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድጓል።
ህብረቱ ድጋፉን ያደረገው በኢትዮጵያ የቡና ምርትን በማስፋፋት የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም ለኦሮሚያ ክልል 18፣ ለደቡብ ክልል 9፣ ለሲዳማ ክልል 3 እና ለአማራ ክልል 3 ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አድርጓል።

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን 4 እንዲሁም ለኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 5 ተሽከርካሪዎችን ህብረቱ አበርክቷል።
ሁሉም ተሽከርካሪዎች በድምሩ በ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ዩሮ ውጭ የተደረገባቸው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን እና የአውሮፓ ኀብረት ተወካይ ሳኔ ዊሊያምስ በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የቡና ምርትን በማሳደግ ሀገሪቱ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል ህብረቱ ያደረገው ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ጠቅሰዋል።

በዘርፉ በተለይ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድርግ እንዲቻል ተሸካረካሪዎቹን ለታለመላቸው የቡና ልማት ማዋል ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የቡና ኤክስቴንሽንን ለማሳለጥ፣ የቡና ችግኝ በብዛት ለማዘጋጀት፣ ቴክኖሎጂን በስፋት ተደራሽ ለማድርግና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ተሽከርካሪዎቹ አጋዥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ህብረት የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ቡድን መሪ ሚስስ ሳኔ ዊሊያምስ በበኩላቸው÷ ህብረቱ በቡና ልማት በተለይም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማሻሻል የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው÷ ባለፉት 40 ዓመታት የቡና ልማትን ለመደግፍ ከ122 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ለአራት ዓመት የሚቆይ የ15 ሚሊዮን ዩሮ የቡና ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን መናገራቸው ኢዜአ ዘግቧል።

በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ እና አማራ ክልሎች በ28 ወረዳዎች የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.