Fana: At a Speed of Life!

ከዛሬ ጀምሮ በየቀኑ ከሳዑዲ በማቆያ ጣብያዎች የነበሩ ዜጎች ይመለሳሉ

 

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ እስከ ስድስት በሚደርሱ የሳዑዲና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በማቆያ ጣብያዎች የነበሩ ዜጎችን የሚመለሱ ይሆናል።

ዜጎችን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሥራ ዛሬ የሚጀመር ሲሆን ቁጠራቸው ከ2ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ከጅዳ ይመለሳሉ።

ቀይ ባህርን በማቋረጥ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሳዑዲ አረቢያን ድንበር አቋርጠው ሲገቡ በሳዑዲ ህግ አስከባሪ አካላት ተይዘው እንዲሁም የመኖሪያ የሥራ ፈቃድ ህግጋትን ተላልፈው በመገኘታቸው በስደተኞች ማቆያ ጣብያዎች ከአንድ አመት በላይ በእስር የቆዩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል።

እነዚህ እስረኞች በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ረዘም ላለ ግዜ በእስር በመቆየታቸው ሳብያ በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቡና ጫና አሳድሮ ከመቆየቱ ባሻገር የአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገርያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

በቅርቡ መንግስት እነዚህ እስረኞች በሙሉ ወደ አገር እንዲገቡ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ብዛት ያላቸው በረራዎች ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመነጋገር የተመቻቸ ነው።

ይህን ለማሳካት ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ ዜጎችን በስፋት ወደ አገር የመመለስ ሂደት ዛሬ ይጀመራል።

በዛሬው ዕለት ቁጠራቸው ከ2ሺ በላይ የሆኑ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ይሆናል።

በራሳቸው ወጪ ወደ አገር ለመግባት ለሚሹ ተመላሾችም በቅርቡ ሁኔታዎች በስፋት ይመቻቻሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በጅዳ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.