Fana: At a Speed of Life!

የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በብዙ መልኩ የተሳካ ነበር – ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በብዙ መልኩ የተሳካ እንደነበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ድምፅ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ቀዳሚ ሪፖርትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ኮሚሽኑ ምርጫውን በሚለከት ባለ 6 ነጥብ አጀንዳ ይፋ አድርጎ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ቀን የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ሲከታተል መቆየቱን ተናግረዋል።

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የሴቶችን ተሳትፎ የማሳደግ፣ ምርጫው አካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በማሳተፍና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ምን ይመስል እንደነበር በትኩረት ክትትል ማድረጉንም አንስተዋል።

በምርጫው መዳረሻ ቀናትና በድምጽ መስጫ እለት 94 ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን በ99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረው የአካባቢ አስተዳዳሮችን፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ሃይሎችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን ማናገራቸውን ጠቁመዋል።

ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት ከመታየቱ በስተቀር በአብዛኛው ቦታዎች የጎላ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመከሰቱን ገልፀዋል።

የምርጫው ዕለት የጎላ ችግር ሳይከሰት በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀበትና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአንፃሩ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው ዕለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው ዕለትና ከድምፅ መስጫ ቀን በኋላ በታጣቂዎች የሰው ህይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ መጉላላትና ማዋከብ መድረሱንም ነው የተናገሩት።

የምርጫ ሂደቱ ለአካል ጉዳተኞች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ተሳትፎ የሚለከቱ ጉዳዮች በቀጣይ መስተካከል እንዳለባቸው አብራርተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.