Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካውያን በጋራ መስራት ለአህጉሩ ቀጣይ እድገት ወሳኝ ነው- ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የላፕሴት ፕሮጀክት አፈጻጸምን በሚዳስሰው ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የተለያዩ የልማት ስራዎችን በጋራ ለመስራት ተግባራዊ በመሆን ላይ የሚገኘው ሲሆን በጉባዔው የሶስቱ ሃገራት የትራንስፖርት ሚኒስትሮች እና ባለሙያዎች ፣የአፍሪካ ህብረት የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
በጉባኤው የሚስተዋሉ ችግሮች በመገምገም የጋራ መፍትሄ ለማምጣት አላማ ያደረገ ሲሆን በመድረኩ ወይዘሮ ዳግማዊት የአፍሪካውያን መያያዝና በጋራ መስራት ለአህጉሩ ቀጣይ ልማትና እድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የላፕሴት ፕሮጀክት በ5 ቢሊየነር ዶላር በሶስቱ ሃገራት የወደብ፣የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የነዳጅ መስመር ዝርጋታ፣ የመንገድና የቱሪዝም ልማትን በመተግበር ሶስቱን ሃገራት በኢኮኖሚ የሚያስተሳስርና በጋራ መልማትን አላማ ያደረገ ፕሮጀክት ነው ተብሏል።
የላፕሴት ፕሮጀክት በስሩ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን የያዘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በ480 ሚሊየን ዶላር በመገንባት ላይ የሚገኘው የላሙ ወደብ አንዱ ነው።
የላሙ ወደብ ፕሮጀክት በሶስት ደረጃ እየተገነባ መሆኑ ተገልፆ የመጀመሪያውን ደረጃ ማጠናቀቅ መቻሉ ተነስቷል።
ይህ ወደብ ሶስቱን ሃገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በቀጠናው ብሎም በአህጉሩ እንደሚፈጥር ታምኖበታል፤ ኢትዮጵያም በወደቡ 20 ሄክታር መሬትን ያገኘች ሲሆን በኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ማልማት እንደምትችል ታውቋል።
በጉባኤው በላፕሴት ፕሮጀክቶች እና በላሙ ወደብ አፈጻጸም ዙሪያ ሶስቱ ሃገራት በሚኒስትሮች ደረጃ ውይይት እየተደረገ ሲሆን በተስተዋሉ ችግሮች በመገምገም የጋራ መፍትሄ ለማምጣት አላማ አድርጓል።
የፕሮጀክቶቹን ቀጣይ ስራዎችን ለማስፈጸም የሚያስችል የፊርማ ስነ ስርዓትም በሶስቱ ሃገራት ዛሬ ይከናወናል።
በፍሬሕይወት ሰፊው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.