Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሙኒራ አል ከሊፋ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና ክልላዊ ጉዳዮች በትብብር መስራት በሚቻልበት ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ፣ ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም መከበር እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እንዲሁም ክልላዊ ትስስርን ለማጠናከር እየተጫወተች ያለውን ሚና በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪ የሁለቱን ሃገራት ትስስር ለማጠናከር በተለይም የእውቀት ሽግግር፣ የዲፕሎማት ስልጠናዎችና ጥናትና ምርምር ዙሪያ ከአቻ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገልግሎት ማሰልጠኛ ተቋም ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ሙኒራ አል ከሊፋ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ አድንቀው የአፍሪካ ቀንድና የመካከለኛው ምስራቅ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር የዲፕሎማቲክ ተቋማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም በቀጣይ ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ጋር በመሆን በዲፕሎማት አቅም ግንባታ፣ የጋራ ምርምር፣ የቋንቋ ስልጠና እና የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተያያዘም አምባሳደሩ ከባህሬን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አቡዱላህ ፋይሰል አል ዶሰሪ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በበይነ-መረብ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደር ጀማል የሁለቱን ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ከዚህ ቀደም የተደረሱ የሰው ሃይል ስምሪት፣ የፖለቲካ ምክክርና ቪዛ ስምምነቶች ወደ ትግበራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደሩ 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ በተመለከተ፣ የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና መቋቋም፣ የሰብዓዊ ፍላጎቶች ለማሟላላት እንዲሁም የሰብዓዊ ጥሰት ለማጣራት እየተደረጉ ያሉ ተቋማዊ እንቅቃሴዎችን በተመለከተ እንዲሁም የህዳሴ ግድብን እና የኢትዮ-ሱዳን የድንበር አለመግባባትን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.